በገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ የተመራ ልዑክ ከደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ጋር በሀገራቱ መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ትብብር ለማጠናከር ያለመ ውይይት አድርገዋል።
ልዑኩ ከኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተላከ መልዕክት ለፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር አድርሰዋል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና በደቡብ ሱዳን የፋይናንስ ተቋማት መካከል ሊኖር ስለሚችል ትብብርም ውይይት መደረጉ ተጠቁሟል።

በተጨማሪ በአየር ትራንስፖርት ዘርፉ ስትራቴጂካዊ አጋርነትን ለማጠናከር ያለመ ውይይት መደረጉም ተገልጿል።
የገንዘብ ሚኒስትሩም አህመድ ሽዴ ኢኮኖሚያዊ ትስስሩን በሚያጠናክሩ በአየር ትራንስፖርት፣ በመሰረተ ልማት እና በነዳጅ ሃብት ጉዳዮች ላይ ጠቃሚ ውይይት ተደርጓል ብለዋል።
የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ለሕዝቦቻቸው የጋራ ጥቅም የሚረዳውን የኢኮኖሚ ትስስር ለማጠናከር ከፍተኛ ቁርጠኝነት እንዳላቸው ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

በተያያዘ የቀጣናዊ ንግድን ለማሳዳግ የሚረዳውን ኢትዮጵያን፣ ደቡብ ሱዳንን እና ጂቡቲን የሚያገናኘው የንግድ እና ትራንስፖርት የኮሪደር ልማትን በተመለከተ ውይይት እንደተደረገበት ታውቋል።
የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ውይይቱ በሀገራቱ መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማሳደግ የሚያስችል ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን አሳውቋል።
ሁለቱ አገሮች በክልሉ ዘላቂ ብልፅግናን ለማምጣት የኢኮኖሚ ውህደትን እና የመሠረተ ልማት ግንባታን ቅድሚያ እንደሚሰጡም የፕሬዚዳንቱ ጽህፈት ቤት ይፋ አድርጓል።