Search

የምርጫ ካርድ ያልዳሰሰው የፖለቲካ ሥልጣን መያዣ መንገድ በኢትዮጵያ ዝግ ነው፦ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ

እሑድ ሰኔ 14, 2018 79

ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት መግለጫ መርሐ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ምርጫው በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ጉዞ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ታየ በንግግራቸው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለምርጫ ያሳየው ከፍተኛ ተሳትፎ የሰላማዊ ሽግግርን ፋይዳ መገንዘቡን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

94 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በምርጫው መሳተፉ፣ የጸብና የአምባጓሮ ባህልን በመተው በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሥልጣንን የመወሰን ፍላጎት እንዳለው በግልጽ ያሳየ ነው ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።

ይህ ከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ያላቸውን ቀናዒነትና ፍቅር በተግባር ያሳዩበት መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ከአሁን በኋላ የሕዝብ ድምፅ ያልጎበኘው፣ የምርጫ ካርድ ያልዳሰሰው የፖለቲካ ሥልጣን መያዣ መንገድ በኢትዮጵያ ዝግ ነው ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ከምርጫ ውጭ በሆነ መንገድ ሥልጣን ለመያዝ ለሚመኙ አካላት መልዕክት አስተላልፈዋል።

አያይዘውም፣ የሀገራችን የፖለቲካ ኃይሎች አካሄዳቸውን ከዘመናዊው የዴሞክራሲ ሥርዓት ጋር እንዲያስተካክሉ አሳስበዋል።

ከሕዝብ ድምፅ ውጭ የሚንቀሳቀሱ አካላት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርሳን "ግርጌ ማስታወሻ" ብቻ የሚቀመጡ እንደሚሆኑም ነው ፕሬዚዳንቱ የጠቆሙት።

የምርጫ ውጤቱ የዜጎች አደራና የክብር ማኅተም መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንት ታየ፣ አሸናፊ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ይህን ከባድ ኃላፊነት በታማኝነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የጸጥታ ኃይሎች፣ መገናኛ ብዙኃንና ታዛቢዎች ለምርጫው ስኬት ላደረጉት አስተዋጽኦ ፕሬዝዳንቱ ምስጋና አቅርበዋል።

የምርጫ ቦርድን የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የተቋማዊ አቅም ግንባታ አድንቀው፣ በቀጣይ ደግሞ የተሻለ ሥራ እንደሚያከናውን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የሚመሩትን አካላት በመምረጡ አሸናፊዎች በታማኝነትና በቅንነት ለሕዝብና ለሀገር እንዲሰሩ አሳስበዋል።

በሃና ምንዳሁን