የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 24 በተካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የተመዘገበውን አጠቃላይ ውጤት ይፋ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ተስፋዬ ንዋይ በሥራ አመራር ቦርዱ የተረጋገጡና የፀደቁ ውጤቶችን ይፋ አድርገዋል።
በዚህም መሰረት ብልፅግና ፓርቲ 438 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎችን አሸንፏል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በተለያዩ አካባቢዎች ባደረገው ተሳትፎ በድምሩ 13 የፓርላማ ወንበሮችን ማግኘት ችሏል።
በተመሳሳይ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ክልል ባደረገው ፉክክር 6 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበሮችን አሸንፏል።
መድረክ በሲዳማ ክልል 3 የፓርላማ መቀመጫዎችን ሲያገኝ፣ ሌሎች ፓርቲዎችም በየክልሉ በወከሉአቸው እጩዎቻቸው አማካይነት የፓርላማ መቀመጫዎችን አግኝተዋል።
የፓርላማ ወንበሮችን ያገኙ የግል ተወዳዳሪዎችም መኖራቸው በመርሐ ግብሩ ላይ ተገልጿል።
የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት ማሳወቂያ መርሐ ግብር ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴን ጨምሮ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ማህበራት ተወካዮች፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን ተወካዮች በተገኙበት እየተካሄደ ነው።
በወንድወሰን አፈወርቅ