Search

ምርጫ ቦርድ ሴቶች ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን እንዲጠቀሙ እና በነጻነት እንዲሳተፉ አዲስ ልምድ ፈጥሯል - የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር

እሑድ ሰኔ 14, 2018 59

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሴቶች ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን እንዲጠቀሙ እና በነጻነት እንዲሳተፉ አዲስ ልምድ መፍጠሩን፣ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ዋና ዳይሬክተር / ሕብረት አባሆይ ገለጹ።

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ጠቅላላ ውጤት ማሳወቂያ መርሐ ግብር ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች እና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተገኙበት እየተካሄደ ይገኛል።

/ ሕብረት አባሆይ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ ማኅበሩ ሁሉም ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን በማረጋገጥ፣ በተለይም ከስጋት ነጻ ሆነው ደኅንነታቸው በተጠበቀ ሁኔታ ምርጫውን በማድረግ ረገድ ያከናወናቸውን ተግባራት በተመለከተ መልእክት አስተላልፈዋል።

በዚህም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫው ወቅት በሴቶች ላይ የሚደርስን ጥቃት ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት የወሰነውን ቅድመ እርምጃ አድንቀዋል።

ቦርዱ ተጎጂን ያማከለ የአሠራር ሥርዓት መመሪያዎችን በማዘጋጀት ተግባራዊ ማድረጉ፣ ሴቶች በዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው እንዲጠቀሙ እና በነጻነት እንዲሳተፉ አዲስ ልምድ መፍጠሩን አመልክተዋል።

መመሪያውንም ተከትሎ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ 10 አባላት የተካተቱበት ብሔራዊ ግብረ ኃይል መቋቋሙን እና በዚህም በሴቶች ላይ ለሚፈጸሙ ጥቃቶች የተሰጠውን ምላሽ ሁሉን አቀፍ እና የተቀናጀ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

በምርጫ ጣቢያዎች ጠንካራ የግንኙነት መሠረት በመዘርጋት ማንኛውም የጥቃት ክስተት በፍጥነት ሪፖርት ተደርጎ በአሠራር መፍትሔ የሚፈልጉ ጉዳዮች ያለመዘግየት መፍትሔ እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።

በመንግሥት ተቋማት፣ በሲቪል ማኅበረሰብ እና በጸጥታ አካላት መካከል የነበረው ትብብር ሴቶች ያለፍርሃት ድምፃቸውን እንዲሰጡ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል ነው ያሉት።

ማኅበሩ ከሁለት የዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር ለምርጫ ታዛቢዎቻቸው አጠቃላይ ሥልጠና መስጠታቸውን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ፣ ይህም ታዛቢዎቹ በምርጫ ወቅት በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመለየትና ለመዘገብ ማስቻላቸውን ጠቅሰዋል።

ማኅበሩ 9 ክልሎች፣ 18 ዞኖች እና 6 ከተማ አስተዳደሮች በሚገኙ 136 የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ሂደቱን ተከታትሏል ብለዋል።

በዚህም 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በአብዛኛው ሰላማዊ፣ ሥርዓት ያለውና ግልጽ እንደነበር ገልጸው፣ 97 ነጥብ 8 በመቶ ሰላማዊ እንደነበርም የምርጫ ታዛቢዎቹ መመዝገባቸውን አመልክተዋል።

ምርጫው ሴቶች ያለ ስጋትና ደኅንነታቸው ተጠብቆ ድምፅ እንዲሰጡ፣ እንዲሁም በአጠቃላይ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲካሄድ ማኅበሩ አስተዋጽኦ በማበርከቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

በአድማሱ አራጋው