የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ11 የምርጫ ክልሎች የድጋሚ ምርጫ እንዲደረግ መወሰኑን ዛሬ ባካሄደው የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት ማሳወቂያ መርሐ ግብር ላይ አስታውቋል።
ውሳኔው የተላለፈው ጉልህ የሆነ የድምፅ አቆጣጠር እና ውጤት አሞላል ችግር በማጋጠሙ እንደሆነ አመልክቷል።
በዚህም የድጋሚ ምርጫው የሚደረግባቸው ሶሮ 1፣ ጠንባሮ፣ ሀርገሌ፣ ዳሮር፣ ሀድጋላ፣ አዋሬ፣ ዳራቶሌ፣ ባቱ (ዝዋይ)፣ ቤጊ፣ አሮሬሳ እና ጨንቻ ምርጫ ክልሎች መሆናቸውን ነው ምርጫ ቦርድ የገለጸው።

በድጋሚ ምርጫው እንዲደረግ ከተወሰነባቸው አምስቱ የምርጫ ክልሎች በሶማሌ ክልል የሚገኙ ሲሆን፣ እነዚህም ሀርገሌ፣ ዳሮር፣ ሀድጋላ፣ አዋሬ እና ዳራቶሌ የተባሉ የምርጫ ክልሎች መሆናቸው ተመላክቷል።
እንዲሁም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሶሬ1 እና ጠምባሮ ምርጫ ክልሎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የድጋሚ ምርጫ ይደረግላቸዋልም ነው የተባለው።
ባቱ (ዝዋይ) እና ቤጊ ምርጫ ክልሎች በኦሮሚያ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች እና ለክልል ምክር ቤት የድጋሚ ምርጫ የሚደረግበት ይሆናል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ጨንቻ ምርጫ ክልል ለክልል ምክር ቤት የድጋሚ ምርጫ እንደሚካሄድም ተገልጿል።
በአድማሱ አራጋው