Search

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ኢትዮጵያውያን ያደረጉት ስኬታማ ተሳትፎ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ትልቅ እርምጃ ነው - የአፍሪካ ህብረት

እሑድ ሰኔ 14, 2018 71

ኢትዮጵያውያን 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ያደረጉት ስኬታማ ተሳትፎ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ትልቅ እርምጃ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን የአፍሪካ ህብረት ታዛቢ ልዑክ እና የህብረቱ የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ደህንነት ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ ገለጹ።የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት የማሳወቂያ መርሐ ግብር በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ፤ ኢትዮጵያውያን 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ያሳዩት ተሳትፎ ለስኬታማ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ትልቅ እርምጃ መጀመራቸውን በተግባር ያረጋገጠ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን እያደረጉት ላለው ለዚህ ስኬታማ ጉዞ የአፍሪካ ህብረት ትልቅ አድናቆት እንዳለው አረጋግጠዋል።

የአፍሪካ ህብረት፣ አባል ሀገራቱ ወደ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር በሚያደርጉት ጉዞ ፍጹም ገለልተኛ፣ ሚዛናዊ እና ነጻ በሆነ መንገድ የመደገፍ ግዴታ እንዳለው ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በቀድሞ የኬንያ ፕሬዚዳንት ዑሁሩ ኬንያታ የሚመራ የህብረቱ የምርጫ ታዛቢ አሰማርቶ እንደነበር አስታውሰዋል።

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ማግስትም የአፍሪካ ህብረት ልዑክ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርትን በማስመልከት መግለጫ ማውጣቱን አስረድተዋል።

ህብረቱ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር ለነበረው ግንኙነት አድናቆታቸውን ገልጸው፤ በዚህች ታላቅ ሀገር ቀጣይነት ላለው መሻሻልና ለዴሞክራሲ መጎልበት በጋራ ለመሥራት ቃል እንገባለን ብለዋል።

አህጉራችን ዴሞክራሲን ከመቀበል ውጪ ሌላ አማራጭ የላትም በማለት፣ ሁሉም የአፍሪካ ሀገራትና ባለድርሻ አካላት ሰላማዊ፣ አካታችና ሙሉ ተሳትፎ የሰፈነበት ዴሞክራሲን ለማስፈን ቁርጠኛ ሆነው እንዲቀጥሉ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።