በአማራ ክልል በዘንድሮው የመኸር ወቅት እስከ አሁን ከ5.4 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል።
የክልሉ ግብር ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ቃል ኪዳን ሽፈራው ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ በክልሉ በ2017/8 የምርት ዘመን የተሻለ የምርት ጭማሪ ለማግኘት ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ስለመሆኑ ገልፀዋል።
በዚህም የሚታረስ መሬትን ሁሉ አሟጦ በማልማት በዘር ለመሸፈን ዓላማ ያደረገ ሥራ መከናወኑንም ነው ምክትል ሀላፊው የገለፁት።
በክልሉ የምርት ጭማሪ የሚሰጡ ዋና ዋና ሰብሎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው ያሉት አቶ ቃልኪዳን፤ በዋናነትም እንደ ስንዴ፣ አኩሪ አተር፣ ማሽላ፣ በቆሎ፣ ጤፍ እና ሰሊጥ ያሉ ሰብሎች ተለይተው መዘራታቸውን ገልፀዋል።
በዘንድሮው የመኸር ወቅት የአፈር ለምነትን እና የማዳበሪያ ግብዓት አጠቃቀምን በማሻሻል የተሻለ የምርት ጭማሪ ለማግኘት ተሠርቷል ያሉ ሲሆን፤ 8.8 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ለማሰራጨት ታቅዶ እሰከ አሁን ከ6.3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ መከናወኑን ተናግረዋል።
በክልሉ ያለውን እምቅ ፀጋ በመጠቀም እና መደበኛ የክላስተር አሠራርን በመተግበር ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ሰብል ለመሸፈን ታቅዶ እስከ አሁን ከ958 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መከናወኑን ገልፀው፤ በምርት ዘመኑ ከ50.3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።
በክልሉ በ2017/8 የምርት ዘመን በጥቅሉ ከ187 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ ነው።
በተስፋሁን ደስታ
#EBCdotstream #AmharaRegion #Agriculture #Meher #Summer