በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና በዳንጎቴ ግሩፕ መካከል ዛሬ የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ የሚገነባው የማዳበሪያ ማምረቻ ኮምፕሌክስ ለሀገሪቱ የግብርና ዘርፍ ከፍተኛ መነቃቃትን የሚፈጥር ነው ሲሉ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሰብል ተመራማሪ የሆኑት አቶ ደስታ ፍቃዱ ገለፁ።
2.5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት እንደሚፈስበት የተነገረለት ሜጋ ፕሮጀክቱ በዓመት እስከ 3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ በማምረት ኢትዮጵያን ከዓለም ግንባር ቀደም የማዳበሪያ አምራቾች መካከል እንደሚያሰልፋት ይጠበቃል።
በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሰብል ተመራማሪው አቶ ደስታ ፍቃዱ ከኢቲቪ ዜና 57 ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለፁት፥ ከኢትዮጵያ አርሶ አደሮች 40 በመቶ የሚሆኑት የአፈር ማዳበሪያን ይጠቀማሉ።
በዓለም ዙሪያ ያሉ አርሶ አደሮች የአፈር ማዳበሪያን በአማካይ 146 ኪ.ግ በሄክታር ሲጠቀሙ፤ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ግን በጣም ዝቅተኛ የሆነውን 35 ኪ.ግ በሄክታር ይጠቀማሉ።
እናም ዛሬ ስምምነት የተፈረመለት የማዳበሪያ ማምረቻ ፋብሪካ በኢትዮጵያ መገንባቱ በሀገሪቱ የግብርና ዘርፍ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች ትልቅ የምስራች ነው።
የማዳበሪያ ፋብሪካ በኢትዮጵያ ስትራቴጂክ ከሚባሉ ኢንቨስትመንቶች አንዱና ዋነኛው ነው ያሉት አቶ ፍቃዱ፤ የሰብል ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።
የአፍሪካ ሕብረት በአቡጃ ስምምነት የማዳበሪያ አጠቃቀምን በ2024 በሄክታር 50 ኪ.ግ በሄክታር ለማድረስ ተልሞ እንደነበር አስታውሰው፤ ሆኖም ግን ይህ እስከ አሁን እውን መሆን አልቻለም ብለዋል።
የአፈር ለምነት ዝቅተኛ መሆን፣ በዝናብ ላይ ጥገኛ መሆን፣ ድርቅና የተፈጥሮ አደጋዎች በዋናነት የሰብል ምርትና ምርታማነት ማነቆዎች መሆናቸውን ያነሱት ተመራማሪው፤ አፈርን በማዳበሪያ አክሞ የአፈር መከላትን በመከላካል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የፋብሪካው መገንባት ወሳኝ ነው ብለዋል።
ፋብሪካው ማዳበሪያን ከውጭ በመግዛትና በማጓጓዝ የሚወጣን ከፍተኛ ሀብት የሚያስቀር ከመሆኑ በተጨማሪ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የማይተካ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
በሃይማኖት ከበደ
#FertilizerComplex #Ethiopia #InvestmentHoldings #DangoteIndustries #foodsecurity #agriculturaltransformation #PMAbiyAhmed