የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር የመከላከል ቡድን 25ኛው የሚንስትሮች ስብሰባ በአፍሪካ የኢኮኖሚክ ኮሚሽን የስብሰባ አዳራሽ ተካሂዷል።
በጉባዔው በክብር እንግድነት የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፤ ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመደገፍ ወንጀሎችን መከላከል ሀገራዊ ሉዓላዊነትን እንደመጠበቅ ነው ብለዋል።
እያንዳንዷ የምትሰረቀው ዶላር የሕፃናት የትምህርት ዕድል፣ የእናቶች ጤና አገልግሎት እና የማኀበረሰቡን የመሰረት ልማት ዕድል የምትዘጋ መሆኗንም አስረድተዋል።
በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ወንጀል መረቦች ዓለም ዓቀፍ ይዘት እንዳላቸው ጠቁመው፤ በፍጥነት እየተስፋፋ በተለያዩ ሀገራት ኢኮኖሚ፣ ሰላም እና ደህነት ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ለተቋሙ ዓላማዎች መሳካት ቁርጠኛ መሆኗን ዳግም ያረጋገጡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ በአባል ሀገራቱ መካከል ትብብርን እና የመረጃ ልውውጥን ማጠናከር ወሳኝ እርምጃ ነው ብለዋል።
ሀገራት ተፈፃሚ ሕግ በማውጣት እና ጠንካራ ተቋማትን በመፍጠር በአጋርነት መሥራት ይገባቸዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ወንጀሉን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚያስችል መሠረታዊ የሕግ ማሻሻናዎችን በማድረግ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሯን ገልፀዋል።
በመድረኩ የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ተገኝተዋል።
በላሉ ኢታላ