የኢትዮጵያ መድን ድርጅት 38ተኛ የሥራ አመራር ጉባዔውን አድርጓል።
በወቅቱ ተቋሙ በ2017 በጀት ዓመት 6.5 ቢሊየን ብር ለካሳ ክፍያ ወጪ ማድረጉን የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቤል ታደሰ አስታውቀዋል።
የካሳ ክፍያ መጠን መጨመሩ የተቋሙ ትርፋማነት ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑንም ገልፀዋል።
በበጀት ዓመቱ ለካሳ ክፍያ ወጪ የተደረገው ገንዘብ ከ2016 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ137.9 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተመላክቷል።
ድርጅቱ በተጠናቀቀው 2017 በጀት ዓመት ከ13.3 ቢሊየን ብር በላይ የአረቦን ገቢ መሰብሰቡን አስታውቋል።
ከተገኘው የአረቦን ገቢ ውስጥ 12.9 ቢሊየን ብር ከጠቅላላ መድን ዘርፍ የተገኘ ሲሆን 248 ሚሊየኑ ደግሞ ከሕይወት መድን ዘርፍ የተገኘ መሆኑን ተገልጿል።
ይህ ገቢ ተቋሙ አገኛለሁ ብሎ በዕቅድ ካስቀመጠው ያነሰ ቢሆንም ከ2016 በጀት ዓመት አንፃር የ56 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።
በ2018 በጀት ዓመት እነዚህ ችግሮች በመቅረፍ አዳዲስ ስትራቴጂዎችን በመቅረፅ ለተቋሙ ለውጥ እንደሚሰራ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገልጸዋል።
በብሩክታዊት አስራት