Search

ማዳበሪያ ማምረት ከምግብ ሉዓላዊነት ጋር የሚያያዝ ነው ፡- የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ

ዓርብ ነሐሴ 23, 2017 50

በኢትዮጵያ ማዳበሪያ ማምረት ከአገር ሉዓላዊነት ጋር የሚያያዝ ነው ሲሉ የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ ተናገሩ።

ሚኒስትሩ በቀጣይ ለመገንባት ስምምነት የተፈረመበትን የማዳበሪያ ማምረቻ ፕሮጀክት አስመልክቶ ከኢቢሲ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ፕሮጀክቱ ማዳበሪያን በአገር ውስጥ አምርቶ በሚፈለገው ጊዜ እና በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የአርሶ አደሩን ምርት ለማሳደግ የሚያስችል ነው ብለዋል።

መንግሥት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እና የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ የጀመረው ጉዞ እንደሚሳካ ፕሮጀክቱ ማሳያ ነው ሲሉ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

ለግብርና ምርት ዋና ግብዓት የሆነውን ማዳበሪያ በአገር ውስጥ አምርቶ የማቅረቡ ሥራ የዘርፉን ሽግግር የሚያፋጥን እንደሆነም አንስተዋል።

ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ ለመፈፀም የሚያስችል የአመራር ቁርጠኝነት መኖሩን የገለፁት ሚኒስትሩ ፥ ይህም በትላልቅ ፕሮጀክቶች በተግባር ታይቷል ብለዋል።

መንግሥት ማዳበሪያ ከውጭ አገራት ገዝቶ ለማስገባት በዓመት የሚያወጣው ወጪ አንድ ነጥብ ሶስት ቢሊየን ዶላር ደርሷል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ማዳበሪያ በአገር ውስጥ መመረቱ የውጭ ምንዛሪን ለማዳን እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ ማዳበሪያ ለመግዛት በውጭ አገራት የሚያጋጥመውን ውጣ ዉረድ የሚያስቀር እና ከአገር ሉአላዊነት ጋር የሚያያዝ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በቀጣይ የዩሪያ ማዳበሪያ ምርትን መነሻ በማድረግ ሌሎች የማዳበሪያ አይነቶችን በአገር ውስጥ በማምረት የግብርና ምርትን ለማሳደግ መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑንም ገልጸዋል።

 

በብርሃኑ አለሙ

#EBC #ebcdotstream #fertilizer