የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በሁሉም የከተማዋ አቅጣጫዎች ወደከተማዋ የሚገቡ፣ ከከተማዋ የሚወጡና በከተማዋ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች፣ ሚኒባሶችና አነስተኛ ሽፍን መኪኖች ላይ የመኪና ኦፕሬሽን ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን ለኢቢሲ ዶትስትሪም በላከው መረጃ አስታውቋል።
ቢሮው እያካሄደ ያለው የመኪና ኦፕሬሽን ሥራ ተሽከርካሪዎቹ ጭነው የሚንቀሳቀሱት ልዩ ልዩ ሸቀጦች፣ ምርቶችና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች በሕጋዊ ግብይት በደረሰኝ የተፈፀሙ ስለመሆናቸው ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑም ተገለጿል።
በዚህም ሳምንት በተካሄዱ የቁጥጥር ሥራዎች በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ 11፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ 4፣ በአቃቂ ቃሊቲ 5፣ በለሚ ኩራ 7 እንዲሁም በጉለሌ 7 ተሸክርካሪዎች ዕለታዊ ደረሰኝ ሳይዙ በከተማዋ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ተገኝተው አስተዳደራዊ የቅጣት እርምጃ የተወሰደ ሲሆን፤ ለጫኑት እያንዳንዱ ዕቃም ደረሰኝ እንዲቆርጡ መደረጋቸው ታውቋል።
በመሆኑም በከተማዋ ጭነት የጫኑ ማንኛውም አይነት ተሽከርካሪዎች፣ ተሳቢዎች፣ ሚኒባሶች እና ሽፍን መኪኖች ለጫኑት እቃ ዕለታዊ ደረሰኝ የተቆረጠበት መረጃ ስለመያዛቸው የማረጋገጥ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብሏል ቢሮው በላከው መግለጫ።
ትልልቅም ይሁኑ ትንንሽ መኪኖች እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ከከተማው ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን ጋር በመቀናጀት ደረሰኝ ስለመያዛቸው የማረጋገጥ፤ ብሎም ያልያዙት ላይ አስተዳደራዊ ቅጣት በመቅጣት ለእያንዳንዱ ለጫኑት እቃ ደረሰኝ እንዲቆርጡ እየተደረገ ነውም ተብሏል።
ስለሆነም ማነኛውም የተሽከርካሪ ባለቤትና አሽከርካሪ እንዲሁም ነጋዴ በመኪና ላይ ጭኖ ለሚያንቀሳቅሰው ማንኛውም ምርት በዕለቱ የተቆረጠ ደረሰኝ የመያዝና ለከተማው የገቢዎች ቢሮ የቁጥጥር ሠራተኞች የማሳየት ኃላፊነት እንዳለበት ቢሮው አሳስቧል።
በሰለሞን ከበደ