የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ያቤሎ የሚያደርገውን በረራ በዛሬው ዕለት ጀምሯል፡፡
የአየር መንገዱ 23ኛ የሀገር ውስጥ መዳረሻ የሆነው የያቤሎ አየር ማረፊያ በሳምንት ሦስት በረራዎችን እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡
የአየር ማረፊያው ስራ መጀመር በለውጥ ጉዞ ላይ የሚገኘውን የቦረና ዞን ለማስተዋወቅ እና የጎብኚዎችን ቁጥር ለመጨመር ከፍተኛ አበርክቶ እንደሚኖረው ተጠቁሟል፡፡
የአውሮፕላን ማረፊያው የቦረናን ባህል፣ ታሪክ፣ የገዳ ሥርዓት፣ የያቤሎን የአዕዋፍ መናኸሪያ፣ የቦረናን ፓርክ ለማየትና ለማድነቅ ዕድል ይሰጣል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከመላ ኢትዮጵያ ጋር በንግድ የተሣሠረው የቦረና ሕዝብ ይበልጥ የሚያስተስስር ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኢትዮጵያውያን በአየር ትራንስፖርት የማገናኘትን ኃላፊነት በተገቢው መጠን በመወጣት ላይ እንደሚገኝ በማንሳትም፤ ከተመረቀው የያቤሎ የአውሮፕላን ማሪፊያ በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልል ብቻ በነገሌ ቦረና እና በጎሬ መቱ አዳዲስ የአውሮፕላን ማሪፊያዎች በግንባታ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ግንባታው 4 ዓመታትን እንደፈጀ የተናገሩት የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፤ 1 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበት አስታውቀዋል፡፡
በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ እና ሌሎችም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
በአሸናፊ እንዳለ
#ebc #ebcdotstream #EthiopianAirlines #yabeloairport