የያቤሎ አውሮፕላን ማረፊያ ከኮንክሪት የተሠራ የአውሮፕላን ማረፊያና ማኮብኮቢያ ብቻ ሳይሆን የህልሞቻችን ማሳኪያ መንገድ ጭምር ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው፤ ለቦረና ሕዝብ አዲስ የተስፋና የልማት መንገድ የሆነውን የያቤሎ አውሮፕላን ማረፊያ መርቀን ሥራ አስጀምረናል ብለዋል።
አውሮፕላን ማረፊያው የሕዝቡን የረጅም ጊዜ የልማት ጥያቄ የመለሰ፣ ታሪክና እሴትን ከነገ መዳረሻ፣ ቅርስን ከዕድገት፣ ሕዝብን ከልማት ጋር ያገናኘ አዲስ የግንኙነት እና የተስፋ አድማስን የከፈተ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
የቦረና ሕዝብ የዳር ድንበራችን ዘብ፣ የጥንቱ የገዳ ስርዓት ጠባቂ፣ የሰላም፣ የሕግ እና የነፃነት አርዓያ ሆኖ ኖሯል ያሉት አቶ ተመስገን፤ አስከፊ ድርቅን በአስደናቂ የውሃ አጠባበቅ ጥበቡ በመሻገር የጽናት ማሳያም ጭምር ሆኗል ብለዋል።
የአውሮፕላን ማረፊያው በቦረና የሚገኙ ውብ የታሪክና የተፈጥሮ ጸጋዎቻችንን ለመግለጥ፣ የገበያ በሮችን ለመክፈት እና የቱሪዝም መዳረሻ መንገዶችን ለመክፈት ትልቅ ዕድልን ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡
የአውሮፕላን ማረፊያው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሀገር ውስጥ የአየር ትራንስፖርትን በማስፋፋት የህዝብን ትስስር እንዲያጠናክርና ለሁሉም የምትመች ሀገር የመገንባት የጋራ ህልምን እንደሚያሳካ ገልፀዋል።
የቦረና ዞንና የያቤሎ ከተማ ህዝብ፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እና ከፍተኛ አመራሮች ላደረጉላቸው አቀባበል ምስጋና ያቀረቡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የያቤሎ አውሮፕላን ማረፊያ ሥራ በመጀመሩ የቦረና እና አካባቢው ህዝብ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
#ebc #ebcdotstream #EthiopianAirlines #yabeloairport