የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 እንዲሳካ እያበረከተ ያለው ድጋፍ የሚደነቅ መሆኑን የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ ገልፀዋል፡፡
የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰውን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡
አየር መንገዱ የፓን አፍሪካ አስተሳሰብን ለዓለም በማስተዋወቅ፣ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል፡፡
አየር መንገዱም ለአህጉሪቱም ኢኮኖሚያዊ ትስስር ወሳኝ ሚና አለው ሲሉ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው አየር መንገዱ አፍሪካን ከዓለም በማገናኘት ትልቅ ሥራ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል::
በአቪዬሽን ዘርፍ አፍሪካውያን ወጣቶችን በማሰልጠን እንዲሁም የተወሰኑ የአፍሪካ ሀገራት አየር መንገዶች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ሁለቱ ተቋማት በአፍሪካውያን መካከል ትስስርን እና የኢኮኖሚ ውህደትን ለማጠናከር በአጋርነት መስራታቸውን እንደሚቀጥሉ ከአፍሪካ ህብረት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በላሉ ኢታላ