Search

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ ያተኮረው “መቻል”- በመሀመድ ሲራጅ

ማክሰኞ ነሐሴ 27, 2017 89

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ መሀመድ ሲራጅ፣ ጋዜጠኛ ሰላም ሙሉጌታ እና ኡመር መኮንን እና ሌሎችም ዕውቅ ኢትዮጵያውያን ያካተተ ቡድን የዲጂታል ዲፕሎማሲ ሰራዊት በመመስረት በሕዳሴው ግድብ ላይ የሚወጡ አሉታዊ ትርክቶችን በማኀበራዊ ሚዲያ የመመከት ሥራ ሲሰሩ እንደነበር የአዋሽ ኤፍ ኤም ሥራ አስፈጻሚ መሀመድ ሲራጅ ይናገራል፡፡

ከዚህ ባለፈ በአዋሽ ኤፍ ኤም የዓባይ ጓዳ የሚል በየቀኑ የሚደመጥ የሬዲዮ ፕሮግራም እንደነበር እና ለ6 ተከታታይ ዓመታትም በተላለፈው ፕሮግራም ስለሕዳሴ በርካታ ሃሳቦች መነሳታቸውን ያስረዳል።

የሕዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ሲጣል ጀምሮ የውስጥ እና የውጭ ጫናው ከሚታሰበው በላይ የከፋ እንደነበር የሚናገረው መሀመድ ሲራጅ፤ ግብጽ ከ358 በላይ የታወቁ የዲጂታል ሚዲያ ሰራዊቶችን አሰማርታ የሕዳሴውን ግድብ ግንባታ ለማስተጎጎል ለአሉታዊ ፕሮፓጋንዳ ትጠቀምበት እንደነበር ይገልጻል፡፡

ጋዜጠኛ መሀመድ ሲራጅ እንደሚለው፣ ግብጽ ሽብር በመንዛት እና የጦርነት ነጋሪቶችን በኢትዮጵያ ላይ በመጎሰም የግድቡን ግንባታ ወደ ኋላ ለመጎተት ብዙ ጥረት አድርጋለች፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በመቋቋም ኢትዮጵያ ስኬት ላይ ደርሳለች ይላል፡፡

ይህንን እና መሰል ሃሳቦችን ለታሪክ ሰንዶ ለማስቀመጥም ያለመ “መቻል” የተሰኘ መፅሐፍ ማዘጋጀቱን ይናገራል።

መቻል የተሰኘው መፅሐፍ እያንዳንዱ የዓረቡ ዓለም ሚዲያ በኢትዮጵያ ላይ ያደረገውን ዘመቻ፣ ላለፉት 13 ዓመታት በተለይም ከለውጡ መንግስት ወዲህ ባሉት ጊዜያት ኢትዮጵያ እንዴት አድርጋ የሕዳሴውን ግድብ እውን ማድረግ ቻለች የሚለውን ዋና ዋና ነጥቦችን ይደስሳል ሲል ያስረዳል።

ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን በሕዝቦቿ ላብ እና የደም ጠብታ ገንብታ ለማጠናቀቅ በምታደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኀበራዊ ጫናዎች ይደርሱባት ነበር የሚለው ጋዜጠኛ መሀመድ ፤  ይህን ሁሉ ፈተና ታልፎ ከስኬት ላይ በመድረሳችን ደስተኛ ነኝ ይላል።

መቻል የተሰኘው መፅሐፌ በቅርቡ ለንባብ ይበቃል የሚለው ጋዜጠኛው፤ የግድቡን ፕሮጀክት ጀምሮ በመጨረስ ሂደት ውስጥ የነበሩ ወጣ ውረዶችን፣ ከውጭ ይነዙ የነበሩ የውሸት ትርክቶችን ምላሽ በመስጠት ሂደት የነበሩ ፈተናዎችን፣ የኢትዮጵያዊያን ጽኑ አቋም በዝርዝር ያስነብባል ሲል ያስረዳል።

መፅሃፉ ከተዘጋጀ 2 ዓመታትን አስቆጥሯል ሲልም ለኢቢሲ ዶትስትሪም ገልጿል፡፡ እንዲህ አይነት የስነ-ፅሁፍ ስራዎች ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንደማያደርስ ለማስረዳት እንደሚያግዙም ነው የተናገረው። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ግድቡ ማንንም እንደማይጎዳ፣የታችውን ተፋሰስ ሀገራት ጭምር ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የመሪነት ጥበብ በተሞላበት መንገድ እውነታውን ለዓለም በማስረዳት ከስኬት ላይ አድርሰውታል ሲል ይገልጻል።

የሕዳሴው ግድብ ተገንብቶ በስኬት መጠናቀቁ ኢትዮጵያ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ጀምራ መጨረስን ለዓለም አሳይታለች ፣ግድቡ ለልጆቻችን ተስፋን እና ብርሃንን ይፈነጥቃል ብሏል ጋዜጠኛ መሀመድ ሲራጅ።

 

በመሀመድ ፊጣሞ