በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እስከ 30 ቢሊየን ብር ድረስ ሕጋዊ ሐዋላን ተጠቅመው ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ የመላክ አቅም ቢኖራቸውም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 6.9 ቢሊየን ብር ብቻ በሐዋላ ወደ ኢትዮጵያ መላኩን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ ገለፁ።
በአቶ አቤ ሳኖ የተመራ የልዑካን ቡድን ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከሚገኙ የዳያስፖራ አባላት ጋር ውይይት አድርጓል።
ከውጭ ከሚላከው ገንዘብ ውስጥ 78 በመቶ በሕገ ወጥ መንገድ እንደሚተላለፍ በጥናት መረጋገጡን የባንኩ ፕሬዚዳንት ለኢቢሲ ተናግረዋል።
በመንግሥት አሰራር መሰረት የውጭ ምንዛሬ ክምችት እየጨመረ ቢሄድም በሕጋዊ መንገድ ከውጭ የሚላከው ግን አነስተኛ እንደሆነ ተጠቁሟል።
በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የሚገኙ ሕገወጥ የገንዘብ አስተላላፊዎች ለዚህ ችግር ዋነኛ ተዋናይ እንደሆኑም ነው አቤ ሳኖ የተናገሩት።
ለቀጣይም በዱባይ ከሚገኙ ሕጋዊ የገንዘብ አስተላላፊዎች ጋር በጋራ ለመስራት ከስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል።
ሕገወጥ ተግባሩን ለመከላከል ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ገንዘባቸውን መላክ እንዳለባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በላሉ ኢታላ
#EBC #ebcdotstream #nationalbank