Search

ኢትዮጵያ ለብሪክስ ፕላስ ስትራቴጂካዊ አጋር

ዓርብ መስከረም 02, 2018 1124

ብሪክስ እና የአፍሪካ አህጉራዊ የነፃ ንግድ ቀጠና (AfCFTA) እርስ በእርስ የሚፎካከሩ ሳይሆኑ፣ አፍሪካን ወደ አዲስ የኢኮኖሚ ጥንካሬ ዘመን ሊያመጡ የሚችሉ አጋዥ ኃይሎች ናቸው።

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነቷን እንዴት ትጠቀማለች የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው። ይህ አጋርነት የምዕራባውያን ጥገኝነትን በብሪክስ ከመተካት ይልቅ፣ የአፍሪካ ኢንዱስትሪዎችን የሚያጠናክር፣ የመሰረተ ልማቶችን የሚያሻሽል እና ቀጣናዊ ንግድን የሚያቀላጥፍ መሆን አለበት።

የኢትዮጵያ ወደ ብሪክስ መግባት፣ 126 ሚሊዮን በላይ ህዝብ፣ እያደገ ያለ የማምረቻ ኢንዱስትሪ እና እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ (GERD) ያሉ ትልልቅ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች አንጻር፣ ወቅታዊ ነው። ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ገበያዎች መካከል እንደ ወሳኝ ማገናኛ ድልድይ ሆናም እየሰራች ነው።

የብሪክስ አባላት በተለይም ቻይና፣ ህንድ እና ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር ቀድሞውንም ጠንካራ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ግንኙነት አላቸው።

ይህ አዲስ አባልነት የቀጣናዊ ውህደትን ያበረታታል። ለምሳሌ፣ የብሪክስ ድጋፍ ያላቸው በኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ መስክ ላይ የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች፣ እንደ የጅቡቲ ኮሪደር እና በድሬዳዋና ሀዋሳ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የአፍሪካ አህጉራዊ የነፃ ንግድ ቀጠናን (AfCFTA) የመገናኛ እና የድንበር ተሻጋሪ ንግድ ማሻሻያ ግቦችን ያሳድጋሉ።

የአፍሪካ አህጉራዊ የነፃ ንግድ ቀጠና AfCFTA የአፍሪካን የእርስ በእርስ ንግድን 2030 50 በመቶ በላይ ሊያሳድግ ይችላል።

ይህንን ለማሳካት ግን የንግድ ስምምነቶች ብቻ በቂ አይደሉም፤ ከፍተኛ የካፒታል፣ የቴክኖሎጂ፣ የመሰረተ ልማት እና የተቀናጀ የፖሊሲ ኢንቨስትመንት ያስፈልጋል።

እንደ ኢንፎብሪክስ ዶት ኦርግ መረጃ የብሪክስ ቡድን በተለይም እንደ አዲሱ የልማት ባንክ (NDB) ባሉ ተቋማት አማካኝነት ከአፍሪካ ውጭ ባሉ የገንዘብ ተቋማት ከሚሰጡ ጥብቅ የብድር ሁኔታዎች ነፃ የሆነ አማራጭ የገንዘብ ምንጭ ይሰጣል።

እንደ ብሪክስ አባል ኢትዮጵያ አሁን ወደ አዲሱ የልማት ባንክ (NDB) የላቀ ተደራሽነት በማግኘት፣ ከአፍሪካ አህጉራዊ የነፃ ንግድ ቀጣና AfCFTA ጋር የሚጣጣሙ እና ለጎረቤት አገራትም አዎንታዊ ተጽእኖ የሚፈጥሩ ፕሮጀክቶችን በገንዘብ መደገፍ ትችላለች።

በተጨማሪም የብሪክስ አባልነት በአፍሪካ የዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ለትብብር ትልቅ እድል ይሰጣል። የብሪክስ አባላት የሆኑት ህንድ እና ቻይና በዲጂታል ቴክኖሎጂ እና በሰፊ ደረጃ ሊተገበሩ በሚችሉ መፍትሄዎች ሰፊ እውቀት አላቸው። የእነሱ ተሳትፎ አህጉር አቀፍ የዲጂታል ገበያ በመፍጠር፣ መሰናክሎችን በማስወገድ እና አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን (SMEs) ወደ ቀጣናዊ የዋጋ ሰንሰለቶች ለማዋሃድ ጠቃሚ ነው።

 

 

በሰለሞን ገዳ