Search

ሕዳሴ - በቀድሞው የፓኪታን ጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ረዳት አንደበት

ቅዳሜ መስከረም 03, 2018 63

የቀድሞው የፓኪታን ጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ረዳት ሻህባዝ ጊል (ዶ/ር) ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ተከታይ ያለው የዩቱዩብ ገፅ አላቸው። በቲክቶክ ደግሞ ከ370 በላይ ተከታዮችን አፍርተዋል።
እኚህ ሰው ታዲያ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አፍሪካውያንን የሚያኮራ ፕሮጀክት ነው ሲሉ አወድሰውታል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ግዙፍ ከሚባሉት የውሃ ኃይል ኤሌክትሪክ ማመንጫዎች መካከል አንዱ የሆነው ሕዳሴ የተገነባው በዓለም አቀፍ አበዳሪዎች ሳይሆን በኢትዮያውያን በራሳቸው አቅም በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ሲሉም ነው የገለፁት።
ግድቡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ብርሃን እንዲያገኙ ከማስቻሉም በላይ ሀገሪቱ ታዳሽ ኃይልን ለጎረቤት ሀገራት በብዛት እንድትልክም ያስችላታል ብለዋል፡፡
 
ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን ውኃ የሚይዝ ኮንክሪት እና ብረት ብቻ ሳይሆን የሉዓላዊነት እና የክብር መገለጫ መሆኑንም አንስተዋል።
ግድቡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት ለመሆን ለያዘችው ትልቅ ሕልም ማሳያ እንደሚሆንም ነው የተናገሩት።
የሕዳሴ ግድብ በመገንባቱ እስካሁን ምንም ዓይነት የውኃ ፍሰት መቀነሱን የሚያሳይ አንዳችም ነገር አለመገኘቱን በገለልተኛ ጥናቶች ተረጋግጧል ሲሉም ሻህባዝ ጊል (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡
እንደ ተንታኙ ማብራሪያ ይህ ሊሆን የቻለው ግን ኢትዮጵያ በዓባይ ተፋሰስ ላይ በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር አማካኝነት ችግኝ በመትከሏ እና በቂ ዝናብ በመኖሩ ነው ሲሉም አስረድተዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ግድቡን በ5 ዓመታት ውስጥ በሂደት በጥንቃቄ እንዲሞላ ማድረጓ ወደታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት የሚወርደው ውኃ እንዳይቀንስ እንዳደረገውም ነው የገለፁት።
ኢትዮጵያ የላይኛው የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት በዓባይ ውኃ እንዳይጠቀሙ የሚከለክል ምንም ዓይነት ዓለም አቀፍ ሕግ አለመኖሩን በተደጋጋሚ መግለጿንም የቀድሞው የፓኪታን ጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ረዳት ሻህባዝ ጊል (ዶ/ር) አስታውሰዋል።
 
በላሉ ኢታላ