በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ እና በአካባቢው በተለያዩ ዓመታት የውኃ ሙላት አደጋ ያጋጥማል።
በተለያዩ ወቅቶችም መንግሥት አደጋውን ለመከላከል እና ተጎጂዎችን ለመደገፍ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ የተመራ ልዑክ በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ የኦሞ ወንዝ ሙላት ያስከተለውን ጉዳት በዘላቂነት ለመፍታት በፌዴራል እና በክልል ደረጃ የተሰሩ ሥራዎችን የመስክ ምልክታ አድርጓል።
የክልሉ የአደጋ ስጋት አመራር ምክር ቤት አባላትም በቱርካና ሐይቅ አካባቢ የሚካሄደው የአደጋ መከላከል ሥራ ያለበትን ደረጃ ተመልክተዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በዚህን ወቅት እንደተናገሩት፤ ቱርካና ሐይቅ እና ኦሞ ወንዝ ሞልተው ወደኃላ የሚፈስሰው የውኃ መጠን ከወትሮው በመጨመሩ ዜጎች ከቀያቸው ለመፈናቀል ተገድደዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመቀናጀት ለዜጎች ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስረድተው፤ ውኃ ሙላቱ የሚያከትለውን ጉዳት ለመከላከል በጊዜያዊ እና ዘላቂ መፍትሄዎች ላይ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ጊዜያዊ መፍትሄው ውኃው አልፎ ወደ ከተሞች እንዳይገባ የመከተር ሥራ ሲሆን ፤ በጥናት በተለየ የመኖሪያ መንደር ተፈናቃዮችን በማስፈር አዲስ ከተማ መቆርቆር ደግሞ ዘላቂ መፍትሄው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ጊዜያዊ መፍትሄ ላይ ጥራት እና ፍጥነት መጨመር እንደሚያስፈልግ በመስክ ምልከታው ገምግመናል ብለዋል፡፡
ለዘላቂ መፍትሄው አስፈላጊ ጥናት ተጠናቅቆ የትግበራ ሥራ እንደሚጠበቅ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለእስከአሁኑ ሥራ ድጋፍ ላደረጉት የፌዴራል መንግሥት እና ሌሎች ባለድርሻዎች ምስጋና አቅርበዋል።
በመስክ ምክልታው በርካታ ቀበሌዎች በውኃው ሙላት አደጋ ውስጥ መሆናቸው ተጠቁሟል።
በውኃው ሙላት ምክንያት እስከአሁን ከ81 ሺህ በላይ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸው ተገልጿል።
ተፈናቃዮችን መልሶ የማደራጀቱ ሥራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚተገበር ክልሉ አስታውቋል።
በተመስገን ተስፋዬ