Search

የሕዳሴ የመሰረት ድንጋይ በተቀመጠበት ቀን የተወለደው አልዓዛር ስለግድቡ ምን አለ?

እሑድ መስከረም 04, 2018 72

አልዓዛር ዐብዮ 14 ዓመቱ ነው።
የተወለደው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ በተቀመጠበት ዕለት መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም. ላይ ነው፡፡
“ኢትዮጵያ ችላለች” በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በአዲስ አበባ በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የተገኘው አልዓዛር ከኢቢሲ ዶትስትሪም ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።
ከግድቡ ጥንስስ ጀምሮ ይሕችን ዓለም የተቀላቀለው ዐዳጊ፤ ዛሬ ላይ ግድቡ ተጠናቅቆ ድሉ ሲበሰር ነብስ ባወቀ አንደበቱ የሀገሩን ባንዲራ ይዞ በደስታ ዘምሯል።
 
የዓባይ ወንዝ ማዕድን እና አፈራችንን ይዞ ወደ ጎረቤት ሀገራት ይጓዝ እንደነበር ከታሪክ አውቄያለሁ የሚለው አልዓዛር፤ ይህ ታሪክ በኢትዮጵያውያን እናት አባቶቼ ድል አድራጊነት በመለወጡ ደስታውን ልካፈል መስቀል አደባባይ ተገኝቻለሁ ሲልም ተናግሯል።
ልደቴን ሳከብርም ሆነ ሌላ ጊዜም የማስበው ስለሕዳሴው ነበር፤ ሕዳሴ ተጠናቅቆ በዓይኔ በማየቴ ደስተኛ ነኝ ብሏል፡፡
ወላጆቼ በሕዳሴው የመሰረት ድንጋይ በተቀመጠበት ቀን እንደተወለድኩ ሲናገሩ በኩራት ነው ያለው አልዓዛር፤ አሁን ደግሞ ግድቡ በመጠናቀቁ ልደቴን በዓመት ሁለት ጊዜ የማከብርበትን ዕድል አግኝቻለሁ ሲል ይገልጻል።
ሕዳሴው ግድብ መጠናቀቁ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያውያን ደስታን የፈጠረ፤ በላብ፣ በደም እና በውሃ ጠብታ የተገነባ ብሔራዊ ሃብታችን ነው ሲልም ነው ያስረዳው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዘርፈ ብዙ አስተዋፅዖ እንሚያደርግ የሚታመነውን ግድብ ከፍፃሜው እንዲደርስ ላደረጉት ጥረት አመሰግናቸዋለሁ ሲልም አልዓዛር ዐብዮ ተናግሯል።
 
በላሉ ኢታላ