የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ "በአዲስ ምዕራፍ ዋዜማ" በሚል ያዘጋጀው የለውጥ ጉዞ ማብሰሪያ መርኃ ግብር እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ ዩኒቨርሲቲዎች የበለጠ ችሎታ ባላቸው የእውቀት ዘርፎች ላይ እንዲያተኩሩ ይደረጋል ብለዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን እና ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ በመሆን 6 አባላት ያሉት እና 9 ወር የፈጀ የለውጥ ጥናት ማካሄዱ ተገልጿል።
በጥናቱ መሰረትም ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲን እንደገና በማደራጀት ለሀገሪቱ ልማት ቁልፍ ሚና የሚጫወት እንደሚደረግ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በመላ ሀገሪቱ እየተገበረው ካለው የሪፎርም ስራ ጋር የተጣጣመ ጠንካራ ሲቪል ሰርቫንት ለማፍራት የሚያስችል ለውጥ ይተገበራል ነው ያሉት።
ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ሁሉንም የትምህርት አይነት ይሰጣሉ ይህ እንደሀገር አዋጪ አይደለም ብለዋል ሚኒስትሩ።
በመሆኑም ዩኒቨርሲቲዎች የበለጠ ችሎታ ባላቸው የእውቀት ዘርፎች ላይ እንዲያተኩሩ የሚያስችል ሪፎርም እየተካሄደ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ንጉስ ታደሰ በበኩላቸው፤ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ እስካሁን እንደነበረው ሳይሆን የልህቀት ተቋም እንዲሆን ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
ለዚህም የሚሆን የአሰራርና የመሰረተ-ልማት ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት በርካታ ቁጥር ያለው ባለሙያዎችን በማስመረቅ፣ በስልጠና እና ምርምሮች አበርክቶ እንደነበረው አስታውሰዋል።
በሞላ ዓለማየሁ
#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #education