Search

የሕዳሴ ግድብ በአፍሪካ ላይ የነበረውን የአትችሉም ትርክት የቀለበሰ ነው፦ ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

ሰኞ መስከረም 05, 2018 59

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በአፍሪካውያን ላይ የነበረውን የአትችሉም ትርክት የቀለበሰ ነው ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ገልጸዋል፡፡
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ከኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካውያን ላይ የሚሰነዘሩ የአትችሉም መንፈስን ከዓድዋ ድል እስከ ሕዳሴ ግድብ በመቀልበስ አሳይታለች ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያውያን የዘመናት ጥያቄ የነበረውን ዓባይን የመገደብ ሕልም በዚህ ዘመን መመለስ ችለናልም ብለዋል፡፡
"የኢትዮጵያን የትርክት ታሪክ ከዓባይ በኋላ እና በፊት ብለን መግለጽ እንችላለን" ያሉት ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ "ይህም ማለት እነሱም አትችሉም ብለው፣ እኛም አንችልም ብለን ነበር፤ ከዓባይ በኋላ ግን እኛ እንደምችል አሳየን፣ እነሱም ትችላላችሁ አሉን" ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን እንደ ጥቁር ፋና ወጊ በመሆን እንደምንችል አሳይተናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ ወደ ከፍታ የመዝለያ ወለላችን በሕዳሴ ግድብ ልክ በመሆኑ የከፍታ ወለላችን ጨምሯል ሲሉ አክለዋል፡፡
ከዚህ በኋላ የምንዘለው እና የምንሻገረው ከሕዳሴው በላይ ባሉ ፕሮጀክቶች ነው ያሉት ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ ለአብነትም ሰባቱን የጉባ ብስራቶችን መውሰድ እንደሚቻል አንስተዋል፡፡
2018 ዓ.ም ለኢትዮጵያውያን አዲስ ዘመን ብቻ ሳይሆን የታሪክ ለውጥ ያመጣንበት ዓመትም ነው ብለዋል፡፡
በሜሮን ንብረት