“ዋሴ፣ ዋሴ” በርካታ አርቲስቶች የተሳተፉበት እና በ17 የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የተዜመ ኅብረ ዜማ ነው።
“ዜማው ሕዳሴ ግድብ መላ ኢትዮጵያውያንን በአንድነት ያስተሳሰረ ሰንደቅ ዓለማ ፕሮጀክት መሆኑን በሚያንፀባርቅ መልኩ የተሠራ በመሆኑ ተወዳጅ ሊሆን ችሏል” ይላል የዜማው ደራሲ አርቲስት ወንድዬ አበበ።
“ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በአንድነት ያስተሳሰረን ዋስትናችን ነው፤ እኔም ይህንኑ ለማመላከት ኅብረ ዜማውን ሠርላችሁ ሲል ለኢቢሲ ዶትስትሪም ተናግሯል።
ከዚህ ቀደም የመከላከያ ሠራዊት አባል የነበረው አርቲስቱ፣ “በእኔ እና በተወለድኩበት አፈር መካከል የሀገር ፍቅር ያበራልኝ መከላከያ ነው” ይላል።
“ሀገርህን ስትወድ ትልልቅ ነገሮችን ታስባለህ፤ መልካም እና በጎ ሐሳብ ከውስጥህ ይመነጫል፤ ፍቅር ትልልቅ ቁም ነገሮችን እንዳስብ እና እንድንቀሳቀስ አድርጎኛል” ሲልም አክሏል።
በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ብዙ ጊዜ ለኢትዮጵያዊነት የሚሰጠው ስም የድህነት፣ የስደት እና የረሃብ ነው የሚለው አርቲስት ወንድዬ፣ በመሰባሰባችን ውስጥ በዓባይ ውኃ ላይ በራሳችን አቅም ሕዳሴን መገንባት እና እውን ማድረግ ችለናል፤ መቻልን በሕዳሴ ያረጋገጥንበት ነው ብሏል።
‘ዋሴ ዋሴ’ የኅብር ዜማ በጥበብ የተሠራውም ዓባይ ዋሳችን፣ ጠበቃችን፣ ምልክታችን ነው የሚለው እሳቤን መሠረት አድርጎ እንደሆነ ጠቅሷል።
“ዓባይ ዘረ-ብዙ ነው፤ ሁሉም ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባላቸው አቅም በጉልበት፣ በገንዘብ ደግፈዋል፤ በእውቀት ያለ ልዩነት ከሕዳሴ ጎን ቆመው በመከራከር የደርሻቸውን ተወጥተዋል፤ እኔም ጥበብን ተጠቅሜ የበኩሌን አድርጌያለሁ፤ በዚህም ደስ ይለኛል” ብሏል።
“እኛ እናልፋለን፣ ሀገር ትኖራለች፤ ሀገር ስትሠራ በቅብብሎሽ ነው። የሆነ አካል ብቻውን ሀገር ሠርቶ አይጨርስም” የሚለው አርቲስት ወንድዬ፣ የኢትዮጵያ መሪዎች የሕዳሴ ግድብን በሐሳብ ከመጠንሰስ እስከ መፈፀም በቅብብሎሽ እዚህ ማድረሳቸው እንደሚያኮራው ነግሮናል።
‘ዋሴ ዋሴ’ ኅብረ ዜማ የዓባይ ውኃ ሙሌት ጀምሮ
እስከ ፍፃሜው ባለው ሂደት በፍቅር እየተደመጠ ብዙዎች ጋር መድረስ የቻለ፤ ሕዝቡ ጋር ሳላወራ ለመግባባት ያደረሰኝ፤ ሕዝቡ ሳይነግረኝ ፍላጎቱን መረዳት የቻልኩበት፤ የላቀ ፍቅር እና ደስታ ያገኘሁበት ዜማ ነው ይላል።የሕዳሴን ከፍታ በ‘ዋሴ ዋሴ’ ኅብረ ዜማ ለመግለጽ የተሞከረበት መንገድ የጥበብ ኃይል አለው።
እግዚአብሔር ሳምሶንን “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘ኃይልህ ያለው በፀጉርህ ላይ ነው፤ ፀጉርህን ጠብቅ’ ብሎታል” የሚለው ወንድዬ፣ የእኛም ትልቁ ኃይላችን ያለው ኅብረታችን እና አንድነታችን ላይ ነው ሲል ይገልጻል።
‘ዋሴ ዋሴ’ የኅብር ዜማ ይህንን ኅብረት እና አንድነት በመጠበቅ የተሠራ በመሆኑ ነው በፍቅር እየተደመጠ ያለው ብሏል።
ዕድር፣ ዕቁብ፣ ጽዋ፣ ቅርጫ፣ ቡና ጠጡ የሚል ማንነት ባለው ማኅበረሰብ ውስጥ በማደጉ ግብረ ገብነትን እንዲላበስ እንዳስቻለው ይናገራል።
“እነዚህ የኢትዮጵያዊነት እሴቶች መገለጫዎች እኔን የቀረጹኝ ይመስለኛል” ሲልም ምስክርነቱን ሰጥቷል።
የጋራ የሆነችው ሀገርን ማስቀደም እና ከነጠላ ማንነት ወደ ብዝኃ ማንነት መግባት በሚጠይቀው ወታደር ቤት ማሳለፉም በእርሱ ማንነት ላይ ትልቅ አሻራ ማሳረፉንም ነው የሚገልጸው።
ሕዳሴ እንደ አየር መንገዳችን እና እንደ መከላከያ ሠራዊታችን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ አንድ ያደረገ የጋራ መገለጫችን ነው ሲል ይናገራል።
ፍፁም አንድነት እና ኅብረት ካለ፣ ምንም ማድረግ እንደሚቻል የሕዳሴው ግድብ ማሳያ መሆኑን ጠቁሞ፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተገንብቶ ለዚህ ፍፃሜ በመድረሱ ደስታዬ እጥፍ ድርብ ነው ብሏል አርቲስት ወንድዬ አበበ።
በመሐመድ ፊጣሞ
#GERD #Abbay #unity #Ethiopia