ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አሁን ካለበት ኃይል የማመንጨት አቅም ላይ እንዲደርስ ካስቻሉት መሠረታዊ ክፍሎች መካከል ኮርቻ ግድብ ዋነኛው ነው።
በሁለት ተራሮች መካከል የተገነባው የኮርቻ ግድብ ፊት ለፊቱ በጥቅጥቅ አርማታ፣ ጀርባው በዐለት የተሞላ በጥበብ እና በከፍተኛ ጥንቃቄ የተገነባ ነው።
ኮርቻ ግድብ በ15 ሚሊዮን ሜትር ኪዮብ የድንጋይ ሙሌት የተገነባ ሲሆን፣ ወደ ላይ 50 ሜትር ከፍታ ያለው፣ እንዲሁም ወደ ጎን 5.2 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ግዙፍ ግድብ በመሆኑ የሕዳሴ ግድቡን አጠቃላይ ከፍታ ከ90 ሜትር ወደ 145 ሜትር ከፍ አድርጎታል።
የሕዳሴ ግድብ ገፀ በረከት የሆነው የኮርቻ ግድብ የግድቡን ኃይል የማመንጨት አቅም ከ 1 ሺህ 400 ሜጋ ዋት ወደ 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት አሳድጎታል።
የኮርቻ ግድቡ ሕዳሴ ከሚፈለገው የውኃ ከፍታ ላይ እንዲደርስ እና የግድቡ አጠቃላይ ውኃ የመያዝ አቅም በአምስት እጥፍ ከፍ እንዲልም አድርጓል።
የኮርቻ ግድቡ ውኃ በማያሳልፍ እና በማያሰርግ መልኩ የተሰራ ቢሆንም የውኃ ስርገትን እና የመሬት ንዝረትን ለመቆጣጠር እንዲሁም ለማጥናት የሚያስችሉ 1 ሺህ 300 ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ያላቸው መሳሪያዎች ተገጥመውለታል።
የግድቡን የውኃ ስርገት ለመከታተል እና የተለያዩ ጥገናዎችን ለማከናዎን እንዲቻል ወደ ውስጥ ዘልቆ ለመግባት የሚያስችል 5 ኪሎ ሜትር የሚሆን ሰው ሠራሽ ዋሻ ያለው የውስጥ ለውስጥ መንገድም ተገንብቶለታል።
የግድቡን አጠቃላይ ውኃ የመያዝ አቅም ከ14 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ወደ 74 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ከፍ ያደረገው የኮርቻ ግድብ ውስጥ የተገነባው ዋሻ በኢትዮጵያ ካሉ ሰው ሠራሽ ዋሻዎች ግዙፉ ነው።
በሕዳሴ ግድብ የተሠሩ አጠቃላይ ሥራዎች 246 ኪሎ ሜትር ወደ ኋላ የተዘረጋ ሰው ሠራሽ ሐይቅ እንዲፈጠር ያስቻሉ ሲሆን፣ ለቱሪዝም ለዓሣ እርባታ እና ለትራንስፖርት አዳዲስ እድሎችን ይዞ መጥቷል።
በሔለን ተስፋዬ
#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #GERD