Search

በሀገሩ ባይተዋር ሆኖ ዝናው በዓለም የናኘው ኢትዮጵያዊው ጌሻ ቡና

እሑድ መስከረም 11, 2018 29

ኢትዮጵያ ስለምታመርተው፣ ነገር ግን በቅጡ ገቢ ስለማታገኝበት ጌሻ ቡና ምን ያህል ያውቃሉ?

ጌሻ ቡና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ጌሻ በሚባል አካባቢ ይበቅላል።

ጌሻ ቡና ጠቀም ያለ የውጭ ምንዛሬ የማስገኘት አቅም ቢኖረውም፤ በተበታተነ ሁኔታ ስለሚመረት በጥቂት ምርት ብቻ ተወስኗል ይላሉ በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉ አካላት።

አጥኚዎቹ እንደሚሉት፥ ጌሻ ቡና በፈረንጆቹ የዘመን ቀመር በ1930ዎቹ ለጥናት በሚል ወደ ፓናማ ተወስዶ አሁን በሀገሪቱ ታዋቂ የቡና ዓይነት ሆኗል።

እናም አሁን ላይ በጌሻ ቡና ከምንጩ ከኢትዮጵያ ይልቅ ወስዳ በማስተዋወቅ የተጠቀመችበት ፓናማ ከገቢ ባሻገር እውቅናም አትርፋበታለች።

ይህ የሆነበት ምክንያት ኢትዮጵያ የራሷን ሀብት በቅጡ ባለማስተዋወቋና ግብይቱን ባለመቆጣጠሯ ነው።

ይህ የቡና ዝርያ አይደለም በዓለም ገበያ እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ እንኳ በአግባቡ የሚታወቅ አለመሆኑ ያስቆጫል።

በአንፃሩ ፓናማ የጌሻን ብራንድ ፈጥራ ከፍተኛ ጥቅም እያጋበሰችበት ትገኛለች።

ፓናማ ጌሻ ቡናን በዓለም ገበያ በኪሎ 1000 የአሜሪካ ዶላር ገደማ በሆነ ዋጋ ትሸጣለች።

የኢትዮጵያ ገበሬዎች በአንፃሩ ይህንኑ ዝርያ በኪሎ ከ3 እስከ 6 ዶላር በሆነ ዋጋ ለዓለም ገበያ ያቀርባሉ።

ኢትዮጵያ ከዚህ የቡና ዝርያ ተጠቃሚ መሆን እንድትችል ቀጥተኛ ንግድን እንዲሁም ዘመናዊ የማስተዋወቂያ ዘዴን ማንበር ይጠበቅባታል።

በፈረንጆቹ 2024 የወጣ መረጃ እንደሚያሳየው፥ ፓናማ 20 ኪሎ ግራም ጌሻ ቡናን በ30 ሺህ 204 የአሜሪካ ዶላር በመሸጥ ክብረ ወሰን አስመዝግባለች።

አሁን ላይ ከፓናማ በተጨማሪ የጌሻ ቡና ዝርያን ተወዳጅነት የተረዱ እንደ ኮሎምቢያ እና ኮስታሪካ ያሉ ሀገራትም በስፋት እያመረቱት ይገኛሉ።

ለዚህ ደግሞ የተሳለጠ መሠረተ ልማት፣ የውጪ ገበያ ትስስር እና የልዩ ዝርያ ቡና ኔትዎርኮችን በስፋት እየተጠቀሙ ነው።

በኃይለሚካኤል አበበ

#GeshaCoffee #GeishaCoffee #Ethiopia #Panama #Colombia