"ያሆዴ" የሀዲያ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል ሲሆን በብሔሩ ተወላጆች ዘንድ ያለ ሀይማኖት ልዩነት በልዩ ድምቀት እና በአንድነት ከሚከበሩ ቱባ በዓላት አንዱና ቀዳሚው ነው።
የሀዲያ ህዝብ የራሱ የሆነ የዘመን አቆጣጠር ያለው ሲሆን፣ የ"ያሆዴ" በዓል ደግሞ አሮጌውን ዓመት ሸኝቶ አዲሱን ዓመት የሚቀበልበት ልዩ በዓሉ ነው።
የያሆዴ በዓል ሀዲያ ዘመኑን የሚቆጥርበት ትልቅ በዓል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከአዲስ ተስፋ፣ ከልምላሜ፣ ለሀገር ሰላም ፀሎት ከማድረግ፣ ከብርሃን ጋር የሚገናኝ ተደርጎም ይወሰዳል።
በዓሉም የክረምቱ ጭጋግ፣ ወንዝ መሙላት አልፎ በፀደይ መባቻ የሚከበር እንደመሆኑ መጠን ብሩህ ተስፋ የሰነቀ፣የብርሃን ጮራ ያዘለ የመልካም ምኞት ማሳያ በዓል መሆኑንም መረጃዎች ያመለክታሉ።
በዓሉ ከመድረሱ አስቀድሞም ሁሉም ሰው የራሱን ድርሻ ለመወጣት ቅድመ ዝግጅት ያደርጋል፤ ከዚያ በኃላ ሁሉም በጋራ በደስታ በዓሉን ያከብራል፤ ፈጣሪውን ያመሰግናል።
ይህ የ"ያሆዴ" በዓል ሲነሳ ሁሌም አብሮ የሚነሳው ያ ሆዴ ጭፈራ (ጨዋታ) ነው።
ጭፈራውን ወጣት ወንዶች በአካባቢያቸው ተሰብስበው በየቤቱ እየተዘዋወሩ ምሽቱን ሙሉ የሚጨፍሩት ባሕላዊ ጨዋታ ነው።
በዚህ ዕለት ማታ ፉኒታ ( ሆያ ሆየ) የሚጨፈርበትና ጨፋሪዎች ደግሞ "ከዚህ ቤት ችጋር ይውጣ፣ በሽታ ይውጣ!" ብለው ችቦ እያቀጣጠሉ ይጨፍራሉ።
ጨፋሪዎች መርቀው ሲወጡ የቤቱ አባወራና እማወራ ደግሞ እናንተም እደጉ በማለት ይመርቁና ይሸኟቸዋል።
ይህ እለት ሁሉም የሀዲያ ሕዝብ የሚመራረቅበት ነው። ያ ሆዴ ጭፈራን ከሌሎች ጭፈራዎች የተለየ የሚያደርገው ልጆች ወላጆቻቸውን የሚመርቁበት በመሆኑ ነው።
በየገቡበት ቤት ሁሉ አተካና እና ለበዓሉ ተብሎ የተዘጋጁ ምግቦችን እየበሉ የቤቱን አባወራንና እማወራ ይመርቃሉ።
ለዚህ በዓል ሴቶችም ከአለባበስ እስከ ፀጉር አሰራር ድረስ በተስተካከለ ሁኔታ ይዘጋጃሉ።
የሀገር ሽማግሌዎች ተሰልፈው ስርአቱን ያስጀምራሉ፤ይከታተላሉ፤ ይመርቃሉ። የሀዲያ ብሔር እሴት የሆነው ያሆዴ ከነሀሴ ወር ጀምሮ በብሩህ ተስፋ የተሞላ ነው። በዚህ በዓል ሴቶች ቀደም ብለው ስራቸውን ይጀምራሉ። ቤታቸውን ያዘጋጃሉ። በህብረት ስራ ይሰራሉ።
ወንዶች ደግሞ እንጨት ያዘጋጃሉ። ሰንጋ ይገዛሉ። ህፃናት ጦምቦራ (ችቦ) ቀድመው ይሰራሉ። በያሆዴ ሰው ብቻ ሳይሆን ከብቶችም አዲስ ዓመት የሚቀይሩበት በመሆኑ ከአምስት ወር ጀምሮ ጥብቅ ወይም ክልክል ሳር ይፈቀድላቸዋል።
በዓሉ ከመከበሩ በፊት በርካታ ዝግጅቶች ይካሄዳሉ። እነዚህም ክንውኖች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው የጎላ እንደሆነ ይነገራል።
የእርቅ ሥነ ሥርዓት
ያሆዴ የተጣላ ታርቆ፣ ያለው ለሌለው አካፍሎ በመተሳሰብ እና በፍቅር መጪውን አድስ ዓመት በደስታ የሚቀበልበት ልዩ የሀዲያ ህዝብ መገለጫ በመሆኑ፣ አስታራቂዎችም ቂም ይዞ አዲስ ዓመትን መቀበል አይቻልም በማለት የተጣሉ ሰዎችን ያስታርቃሉ።
በሀዲያ አዲስ ዓመትን ያሆዴን ለመቀበል በቅድሚያ አንድ ሰው ከተጣላው ጋር እርቀ ሰላም ማውረድ አለበት። ቂም ይዞ አዲሱን ዓመት መቀበልም ሆነ ማንኛውንም ዓይነት ዝግጅት ማድረግ አይችልም።
በርካታ የሀገር ሽማግሌዎችም እየዞሩ የተጣላን ያስታርቃሉ። ታዲያ የተጣሉ ሕፃናትም ቢሆኑ ተፈላልገው ይታረቃሉ። ወይንም አስታርቁኝ ብለው እኩዮቻቸውን ይልካሉ። ይህም ሁኔታ በማህበረሰቡ ዘንድ መረጋጋት እንዲኖር ከማድረጉ አኳያ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል።
ከዚህ በዓል ማግስት ጀምሮ የሀዲያ ህዝብ የመረዳዳት ባህሉን በስፋት የሚያንፀባርቅበት፣ ጥልንና ቂምን በማስወገድ በአዲስ መንፈስ በማህበረሰቡ መካከል ግንኙነትን በማጠናከር እንደ ቤተሰብና እንደ አካባቢው እቅዶች ተለይተው የሚታረቁበት፣ እንደ ማህበረሰብ እንዴት መለወጥ እንዳለባቸው የሚመካከሩበትና አቅጣጫ የሚይዙበት በመሆኑ ማህበራዊና ባህላዊ ጥቅሙ የጎላ ነው።
እንዲሁም በልማት፣ በግብርና፣ በንግድና በሌሎች ስራዎች ላይ የሚመክሩበት በዓል ነው።
ለስራው ባለው ትጋት እንደምሳሌነት የሚጠቀሰው የሀዲያ ህዝብ ለስራ ከተሰማራባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ከሀገር ውጭም ሳይቀር ያሆዴ በዓልን ከቤተሰብ፣ ከዘመድ አዝማድ፣ ከአብሮ አደግና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር አብሮ ለማክበር ወደ ሀዲያ ይተማል።
በአሉን ለማክበር በወርሀ መስከረም መግቢያ ላይ ወደ ሀዲያ ምድር የሚተመው አውቶቡስ፣ ሚኒባስ የግል መኪና ቁጥር በቀላሉ ሊጠቀስ የማይችል ነው። ይህ እውነታም በሙዚቃና በሥነ ቃል ጎልቶ ይታያል።
ያሆዴ ያ ሆዴ ያሆዴ…… ያሆዴ ሆ ያሆ
ዱቢንሴ ኢንጃ ጉሎ………ዴ ሆ ያሆ
ባሪንሴ ዋሳ ጉሎ………..ያሆዴ ሆ ያሆ በማለት ያዜማሉ።
ትርጓሜውም ከጓሮ ቅመም ጨራሽ ከጉድጓድ ቆጮ ጨራሽ እንደማለት ነው።
የእብድ ገበያ አንዱና ዋነኛው የ ያሆዴ በዓል ከሚከበርበት ዕለት ከአስራ አምስት ቀናት አስቀድሞ የሚጀመረው ‹‹የመቻዕል ሜራ›› የበዓል ዝግጅት የሚደረግበት ገበያ ነው።
መቻዕል ሜራ የሚለውን ቃል የያዘውን ፅንሰ ሀሳብ በአቻ ለመግለጽ አስቸጋሪ ቢሆንም ሀሳቡ የእብድ ገበያ እንደማለት ነው። በያሆዴ የእብድ ገበያ አንዱ አካል ነው።
ይህ ስርአት በብሔሩ ባህላዊ አንድምታ ያለውና የገበያ ተጓዦች ስርአት ሲሆን፤ ከትውልድ ቀያቸው እርቀው የሚኖሩትን የማህበረሰብ አካላት ሳይቀር የሚያገናኝ የበዓል ገበያ ነው። በዚህ ገበያ ፈጣሪ ይመሰገናል።
ሁሉም ሰው ገበያውን ይጎበኛል። ታዲያ በዚህ የዕብድ ገበያ የማይሸጥ የማይለወጥ ነገር የለም። ገበያ ገብቶ የለም የሚባል ቃል አይሰማም። ስያሜውም የእብድ ገበያ እንደመሆኑ ከሌሎች የገበያ ቀናት የሚለየው የራሱ የሆኑ በርካታ መገለጫዎችና ክንዋኔዎች አሉት።
የእብድ ገበያም የሚል ስያሜ ያሰጠው ገበያው የሚደራበት ሰዓት ከወትሮው የተለየ በመሆኑ ነው። በዚህ ወቅት ጊዜ ውድ በመሆኑ ከጠዋቱ በአስራ ሁለት ሰዓት ገበያው በመድራቱ ነው። በዚህ ሰዓትም መገበያየት ይጀመራል።
ሌላው ደግሞ እንደመደበኛ እስከ ማታ አለመቆየቱ ነው። ከቀኑ በስድስትና በሰባት ሰዓት ሰው ተገበያይቶ ገበያው ይበተናል።
ይህም ገበያ የሀዲያ አባቶች "ጊዜውን እንዴት እንጠቀም" በሚል በባህላዊ ጥበብ የተቀነባበረ የጊዜ አጠቃቀምን የሚያሳይ ነው። በዚህ ገበያ አባወራ በእብድ ገበያ ከቀረቡ ሰንጋዎች መካከል መርጦ ቀልቡ ያረፈበትን ሰንጋ ሙሉ ብር እንኳን ባይኖረው ገዝቶ የሚወስድበት ባህላዊ የግብይት ሥርዓት ነው።
ምንም ብር ከሌለው ደግሞ ከመጣበት አካባቢ የአንዱን ታዋቂ ሰው ስም በመጥራት ቀልቡ ያረፈበትን ሰንጋ ያለ ምንም ተያዥ ይዞ ይሄዳል። ቀሪውን ብር ደግሞ በአዝመራ ወቅት ይከፍላል።
በዚህም መሰረት ለያ ሆዴ የወሰዱትን ሰንጋ ከህዳር እስከ ጥር ባለው ወራት ውስጥ በታማኝነት ተከፍሎ ያልቃል። በዕብድ ገበያ እናቶች ለያሆዴ በዓል አተካና ለማዘጋጀት የሚጠቅሙ የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችን የእንሰት ተዋፅኦ ማለትም እንደ ቡላ፣ ቆጮ እንዲሁም ቅቤና አይብ ያዘጋጀሉ።
እንዲሁም ናቆሮ (ዳጣ) ለማዘጋጀት ደግሞ ነጭ ሽንኩርት፣ዝንጅብል፣ ዛላ በርበሬ፣ ቀይና አረንጓዴ ሚጥሚጣ በበቂ ሁኔታ ያዘጋጀሉ። በአሉ ካለፈ እስከ መስከረም ሰላሳ ገበያ ስለማይቆም የግብይቱ ሂደት ይህንን ታሳቢ ያደረገ ነው።
አተካና
በዓሉን አስመልክቶ የሚኖረው ቅድመ ዝግጅት ለያሆዴ ክብረ በዓል አንዱ የሆነው የአተካና ወይም የአተካኒሞ ምሽት ተጠቃሽ ነው። ያሆዴ አንድ ተብሎ መከበር የሚጀምረው አተካኒሞ ከበዓሉ አንድ ቀን በፊት አዛውንቶች ችቦ በማቃጠልና አተካናን በመቅመስ ነው።
አተካና የሀዲያ ባህላዊ ምግብ ነው። በብዛት የሚዘጋጀው ለያሆዴ ሲሆን፤ ብዙ ጊዜ ለእንግዳ የሚቀርብ ነው። አሰራሩም በጥንቃቄና በስርአት ሲሆነ ከተሰራ በኋላ ከአንድ ወር በላይ መቆየት ይችላል። በያሆዴ አተካናን አለማዘጋጀት አይቻልም።
የሚሰራው ከቆጮ፣ ቡላ፣ ከቅቤ፣ አይብ፣ ወተትና ከተለያዩ ቅመማ ቅመሞች ነው። ስራውም አድካሚና ጥራትን ስለሚፈልግ ቀደም ብሎና በሕብረት መሰራት ይጀምራል።
በዚህ ሥራ ላይ እንሰት ፍቆ ቡላ ከማዘጋጀት አንፃር በተለየ ሁኔታ ልጃገረዶች ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል። አተካና የዘመን መለወጫ ቀንን አመላካች ነው። በበዓሉ እለት ለሚመጣ እንግዳና ማታ ለጭፈራ ለሚመጡ ህፃናት አተካና የግድ ይሰጣል።
በአቅም ምክንያት አተካናን እንኳን ማዘጋጀት የማትችል ሴት ካለች የአካባቢው ነዋሪዎች ለአተካና መስሪያ የሚያስፈልጉ ነገሮችን በማጠራቀም ይሰጣሉ። በዓዓሉም የሁሉም ሰው ደስታ ሆኖ ያልፋል።