የትግራይ ሕዝብ ሰላምና ልማትን እጅግ የተጠማ ቢሆንም ይህን መሻቱን ማሳካት የሚችለው ግን ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት በነበረ ኋላቀርና አሮጌ አስተሳሰብ ከተተበተበው ህገወጡ የህወሓት ቡድን መላቀቅ ሲችል ነው።
ይህ ህገወጥ ቡድን ለትግራይ ሕዝብ ልማትና ብልጽግና ማምጣት ቀርቶ የራሱን ሕልውና ማቆየት የማይችል ማፊያና ወንጀለኛ ስብስብ መሆኑን በተግባር እያሳየ ይገኛል።
የህወሓት ቡድን ከሃምሳ ዓመት በፊት በነበረውና ጊዜው ባለፈበት ኮሚኒስታዊ አስተሳሰብ ላይ ተቸንክሮ የቀረ "ቆሞ ቀር" ኃይል ነው። ዓለም በቴክኖሎጂ፣ በሐሳብ ልዕልና እና በዲሞክራሲያዊ ውይይት ወደፊት በሚገሰግስበት በዚህ ዘመን ቡድኑ አሁንም የሙጥኝ ያለው ያረጀና የሞተ ሐሳብን ነው።
ይህ ቡድን የራሱን ጠባብ ፍላጎት በሌሎች ላይ በጉልበት ለመጫን ሲል ብቻ የትግራይን ሕዝብ ወደማያስፈልግ አውዳሚ ጦርነት አስገብቶታል። አሮጌ አስተሳሰብ ሁልጊዜም መፍትሔ የሚፈልገው በጠመንጃ አፈሙዝ በመሆኑ ቡድኑ ሰላምን እንደ ስጋት፣ ጦርነትን ደግሞ እንደ ብቸኛ የህልውና ማረጋገጫ አድርጎ ወስዶታል።
የዚህ ቡድን ፖለቲካዊ ኪሳራ በግልጽ የሚታየው በወጣቶች ላይ እየፈጸመ ባለው ማፊያዊ ተግባር ነው። ሰላምና ልማት የናፈቀውን የትግራይን ወጣት በግዳጅ ለጦርነት በማሰለፍ፣ በማስገደድና በማፈን የጦርነት ማገዶ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
ከዚህም አልፎ የቡድኑ ወንጀለኝነት ጣሪያ የነካው ወጣቶችን ለውጭ ኃይሎች በቅጥረኛ ተዋጊነት አሳልፎ በመሸጥ የደም ገንዘብ የሚሰበስብ ማፊያዊ ድርጅት መሆኑ ነው። ይህ የሰው ልጅን እንደ እቃ የመነገድ ድርጊት የትግራይን አምራች ኃይል በማምከን፣ የወደፊት ተስፋውን የማጨለም ሆን ተብሎ የሚሰራ የታሪክ ወንጀል ነው።
የገዛ ወገኑን ለቅጥረኛ ውጊያ ለባዕዳን የሚሸጥ ቡድን ስለ ሕዝብ ጥቅም ሊቆረቆር ቀርቶ፣ የፖለቲካ ሞራልም ሆነ ሰብዓዊነት የሌለው የጥፋት ማሽን መሆኑን ያረጋግጣል።
የትግራይ ሕዝብ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሰላምና ልማት ይገባዋል። በሌሎች የአገራችን ክፍሎች እየታዩ ያሉ የልማት ጸጋዎች በትግራይም መሬት መንካት አለባቸው።
ይሁን እንጂ በአሮጌ አስተሳሰብ አዲስ ልማት ስለማይመጣ፣ የተዘጋ አእምሮ ያለው ቡድን የሕዝብን የኢኮኖሚ ጥያቄ ሊመልስ አይችልም። ጦርነትና ብልጽግናም አብረው አይሄዱም፤ ፖለቲካዊ ቁማሩን በወጣቶች ደም ላይ የገነባ ቡድን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ብልጽግናን ሊያረጋግጥ ከቶውንም አይችልም።
"ላም እሳት ወልዳ እንዳትልሰው እሳት ሆነባት እንዳትተወው ልጅ ሆነባት" እንደሚባለዉ የትግራይ ሕዝብ አጣብቂኝ፣ ይህ የጥፋት ኃይል እስካለ ድረስ የሚቀጥል አዙሪት ነው።
ይህ ሁሉ መስዋዕትነትና የሕይወት መጥፋት ሊቆም የሚችለው፣ የፖለቲካው መሪነት ከትላንት እስረኞች እጅ ወጥቶ የነገ ራዕይ ያላቸው የተማሩ ወጣቶች ሲረከቡ ብቻ ነው። በመሆኑም የትግራይ ወላጆች ልጆቻቸውን ከጦርነት እሳት በመታደግ ስልጣን ለተማሩ ልጆቻቸው እንዲያስረክቡና ሕዝባችን ሰላም ይገባዋል ብለው በቆራጥነት ሊጠይቁ ይገባል።
በተጨማሪም በኢትዮጵያ ያለውን የፖለቲካ ስብራት በዘላቂነት ለመጠገን የተጀመረዉ አገራዊ ምክክር ጉባኤ ትልቅ ዕድል በመሆኑ የትግራይ ሕዝብም ሆነ የተማረው ወጣት ከጠመንጃ ፖለቲካ በመውጣት የራሱንና የአገሩን ዕጣ ፈንታ በሰላማዊ መንገድ መወሰን አለበት።
የህገወጡ ህወሓት የቆሞ ቀርነት፣ የጦርነት አባዜ እና ማፊያዊ የሰው እልቂት ንግድ ማብቂያው አሁን ሊሆን ይገባል። የትግራይ ሕዝብ ዳግም ወደ ግጭት የሚያስገባውን አሮጌውን ኃይል አስወግዶ፣ ዘመኑን ከሚዋጅና አገርን ከሚገነባ አዲስ የተማረ የለውጥ ኃይል ጋር ሊቆም ግድ ይለዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: