Search

በዜጎች ክንድ የሚገነባ ሀገር፡- የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜግነት ድርሻ

እሑድ ሐምሌ 19, 2018 73

 

በየዓመቱ የክረምት ወራት ሲመጣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ድምቀት ልዩ ነው። ዝናቡና ቅዝቃዜው ሳይበግረው ሚሊዮኖችን የሚያንቀሳቅሰው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ በአሁኑ ወቅት የሁለንተናዊ እድገት ዋና አንቀሳቃሽ ሞተር ለመሆን በቅቷል።

አገልግሎቱ ወጣቶችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እውቀታቸውን፣ ጉልበታቸውንና ጊዜያቸውን አስተባብረው ለሀገራቸው የሚለግሱበት ታላቅ መድረክ ነው።

የዚሁ በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ ግብር በኅብረተሰቡ ሁለንተናዊ ሕይወት እንዲሁም ከመንግሥት ካዝና ሊወጣ የሚችለውን ከፍተኛ ወጪ በማስቀረት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያበረከተ ይገኛል።

በዚህም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በቀጥታ የኅብረተሰቡን መሠረታዊ ፍላጎቶች በመመለስ ፈጣንና የሚጨበጥ ለውጥ እያስመዘገበ ነው።

በሌላ በኩል በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የሚሰጠው የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት የተማሪዎችን የትምህርት አቀባበል ከመደገፍ ባሻገር፣ የግል አጋዥ አስተማሪዎችን መቅጠር ለማይችሉና አነስተኛ ገቢ ላላቸው ወላጆች ትልቅ እፎይታ ሰጥቷቸዋል።

እንዲሁም በደም ልገሳ፣ በነፃ የሕክምና አገልግሎት፣ በጽዳትና የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች አማካኝነት በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚከሰቱ የተላላፊ በሽታዎችን ስጋት በመቀነስ ረገድ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው።

የአረጋውያንንና የአካል ጉዳተኞችን መኖሪያ ቤቶች ማደስ፣ የምግብና የማኅበራዊ ድጋፍ ማድረግ አብሮነትንና ማኅበራዊ ትስስርን በማጠናከር ረገድም የራሱን ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማህበራዊ ፋይዳው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በቢሊዮን የሚቆጠር የመንግሥትን በጀት በመታደግ በኩል የሚያበረክተው አስተዋጽዖ እጅግ ከፍተኛ ነው። የመንግሥትን ውስን ሀብትም በሌሎች ልማቶች ላይ እንዲያውል ትልቅ ዕድል መፍጠር ችሏል።

አቅም የሌላቸው ወገኖችን ቤቶች ማደስ፣ የችግኝ ተከላና የእንክብካቤ ሥራዎች፣ እንዲሁም አነስተኛ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እንደ መንገዶች ጥገና እና የድልድይ ሥራዎች በመንግሥት መደበኛ በጀት ቢከናወኑ ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅ ቢሆንም፣ የበጎ ፈቃደኞች የጉልበትና የእውቀት አስተዋጽዖ ይህንን ወጪ በቀጥታ ያስቀራል።

በትምህርትና በጤና ዘርፍ የተሰማሩ በጎ ፈቃደኞች የሚያበረክቱት አገልግሎት የመንግሥትን ተጨማሪ የሰው ኃይል ቅጥርና የትርፍ ሰዓት ክፍያ ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል።

በመሆኑም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በገንዘብ ሊሰላ የማይችል የዜጎችን ጉልበትና እውቀት ወደ ሀገራዊ ሀብት የሚቀይር አሠራር ነው።

የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰብዓዊነትን፣ ሀገር ወዳድነትንና ቁሳዊ ጥቅም-አልባ አገልግሎትን የሚያስተምር ትልቅ የትውልድ መቅረጫ መድረክ ነው። ይህ እንቅስቃሴ ለኅብረተሰቡ አፋጣኝ ማኅበራዊ መፍትሔዎችን ከመስጠት ባሻገር፣ የመንግሥትን የፋይናንስ ጫና በመቀነስ ረገድ የጎላ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

ይህንን በጎ እሴት በተደራጀ መንገድ ማስቀጠልና የሥራዎቹን የጥራት ደረጃ የበለጠ ማሳደግ፣ የሀገራችንን የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ጉዞ በእጅጉ ያፋጥነዋል።

በአድማሱ አራጋው

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: