ኢትዮጵያ 40 ሀገራትና 26 ዓለም አቀፍ የኢንዱስትሪ አጋሮች የሚሳተፉበትን በአኅጉሪቱ ከፍተኛ ትኩረት የሚስብ የሎጂስቲክስና የኮሙኒዩኬሽን ሲምፖዚየም ከነገ ጀምሮ እስከ ሐምሌ 25 ታስተናግዳለች።
የመከላከያ የውጭ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ እና በአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ (አፍሪኮም) የሎጂስቲክስ ዳይሬክተር ብርጋዲየር ጀነራል ፖውል ፍሊክ ዝግጅቱን በማስመልከት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ሜጀር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ በዚሁ ወቅት፣ ኢትዮጵያ ለዚህ ታላቅ አኅጉራዊ መድረክ አስተናጋጅ ሆና መመረጧ በቀጣናው ለሰላም ያበረከተችው አስተዋፅኦ፣ በመንግሥት የተመዘገበው የልማት ውጤት፣ የአዲስ አበባ ከተማ እያሳየች ያለው ፈጣን ዕድገት እና ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን የማስተናገድ አቅሟ የፈጠረው ውጤት መሆኑን ጠቁመዋል።
ሲምፖዚየሙ በአሜሪካና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ትብብር የሚያጠናክር ከመሆኑም በላይ፣ በአፍሪካ የመከላከያ ተቋማት መካከል የልምድ ልውውጥና የጋራ ትብብር የሚያጎለብቱበት መድረክ መሆኑን አመልክተዋል።
ሎጂስቲክስና ኮሙኒዩኬሽን በማንኛውም ወታደራዊም ሆነ ሰላማዊ ተልዕኮ ስኬት ውስጥ ወሳኝ ሚና ያላቸው ዘርፎች መሆናቸውን የገለጹት ሜጀር ጄኔራል ተሾመ፣ ተሞክሮዎችን በመለዋወጥ፣ የተሻሉ አሠራሮችን በመቅሰም እና ለወደፊት የሚያጋጥሙ የሎጂስቲክስና የኮሙኒዩኬሽን ችግሮች የጋራ መፍትሔ ለማፈላለግ ወሳኝ አጋጣሚ መሆኑን አብራርተዋል።
ከአጋር ሀገራት የሚገኙ ልምዶችና ዕውቀቶች ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሎጂስቲክስና የኮሙኒዩኬሽን አቅምን ለማሳደግ ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸውም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ያላትን ልምድ ለአጋር ሀገራት በማካፈል በአኅጉራዊ ሰላምና ደኅንነት ዘርፍ ያላትን አስተዋፅኦ የበለጠ እንደምታጠናክርም አስገንዝበዋል።
ብርጋዲየር ጀነራል ፖውል ፍሊክ በበኩላቸው፣ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር በመተባበር የ2026 የአፍሪካ ሎጂስቲክስና ኮሙኒዩኬሽን ሲምፖዚየምን በጋራ በማዘጋጀቷ ከፍተኛ ደስታና ክብር እንደሚሰማቸው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለሲምፖዚየሙ መሳካት ያደረገችውን ዝግጅት አድንቀው፣ ኮንፈረንሱ በአሜሪካና በአፍሪካ መካከል በሎጂስቲክስና በኮሙኒዩኬሽን ዘርፍ ያለውን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር እንደሚሆን ጠቁመዋል።
በቀጣዮቹ ቀናት ተሳታፊ ሀገራት የሎጂስቲክስና የኮሙኒዩኬሽን አቅሞቻቸውን በመገምገም፣ ያሉ ክፍተቶችንና ተግዳሮቶችን በጋራ በመለየት ዘላቂ መፍትሔዎችን ለማፍለቅ እንደሚሠሩም አስረድተዋል።
ሲምፖዚየም በትብብር፣ በፈጠራና በጋራ ትምህርት የተሞላ ፍሬያማ ሳምንት እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸው፣ በጋራ በመሥራት ጠንካራ የትስስር መረቦችን በመገንባት የሀገራትን አቅም ከፍ ማድረግና ለበለጠ ደኅንነትና ብልጽግና መሠረት መጣል እንደሚቻል መናገራቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለኢቢሲ በላከው መረጃ አመላክቷል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: