የሀገራት ዲፕሎማሲዊ ግንኙነቶች ለዘመናት በመዝጊያ አዳራሾች በሚካሄዱ ውይይቶች፣ የስምምነት ሰነዶች እና የመንግሥታት መግለጫዎች ሲካሄዱ ቆይተው፣ ዛሬ ላይ ዓለም አዲስ የዲፕሎማሲ ቋንቋ እየተማረች ትገኛለች። የዚህ ቋንቋ ፊደላት የዛፍ ቅጠሎች ሲሆኑ፣ የሚጻፈውም በምድር ላይ በሚገኙ የእጆች ዐሻራ ነው።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሯ የፈጠረችው ይህ አዲስ አካሄድ፣ የአካባቢ ጥበቃን ከዲፕሎማሲ ጋር በማጣመር "ኢኮ-ዲፕሎማሲ" የሚባል አዲስ የለውጥ ባህል እየገነባች መሆኗን ያሳያል። ይህ አካሄድ ከሀገር ወደ ሀገር የሚላኩ መልዕክቶች በቃላት ብቻ ሳይሆኑ በተግባርም እንዲገለጹ አድርጓል።
በቀደሙት ዓመታት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የውጭ ሀገር መሪዎችና ከፍተኛ ባለስልጣናት ጉብኝታቸውን በውይይትና በስምምነት ብቻ ያጠናቅቁ ነበር። ዛሬ ግን የጉብኝታቸው መጨረሻ አረንጓዴ ዐሻራ በማስቀመጥ እየተጠናቀቀ ነው። ይህም ለትውልድ የሚቆይ የወዳጅነት፣ የሰላምና የጋራ ኃላፊነት ምልክት ሆኗል።
በቅርብ ጊዜም ወደ ኢትዮጵያ የመጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሏቸው ዓለም አቀፍ የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በመሳተፍ ችግኝ ተክለዋል።
ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ መልዕክቷን በመደበኛ የዲፕሎማሲ መስመሮች ብቻ ሳይሆን፣ በዲጂታል ዓለምም እንድታደርስ እድል ፈጥሯል። እነዚህ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የተከሉት አንድ ችግኝ በሚያጋሩት ምስልና ቪዲዮ አማካኝነት የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ልማት ለዓለም የሚያስተዋውቅ ሆኗል።
በሌላ በኩል የሀገር ውስጥ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ አርቲስቶች፣ ስፖርተኞች፣ ተማሪዎችና መላው ኅብረተሰብ በየዓመቱ በአረንጓዴ ዐሻራ በመሳተፍ ይህን ተግባር ከመንግሥት ፕሮጀክት ወደ ሕዝባዊ ባህል ቀይረውታል። ይህ ደግሞ አረንጓዴ ዐሻራ የሁሉም ዜጋ የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ያረጋግጣል።
ከአካባቢ ጥበቃ በተጨማሪ አረንጓዴ ዐሻራ ለኢትዮጵያ የለስላሳ ኃይል (Soft Power) መሳሪያም ሆኗል። ሀገራት የሚያገኙት ተፅዕኖ በኢኮኖሚና በወታደራዊ ኃይል ብቻ እንዳልሆነና በአካባቢ ጥበቃ፣ በአየር ንብረት እርምጃ እና በሰብዓዊ እሴቶችም ሊገነባ እንደሚችል እያሳየ ይገኛል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ለሀገራት ተሞክሮ የምታካፍል ሆናለች። ይህ ተነሳሽነት የዛፍ ተከላ ዘመቻ ብቻ ሳይሆን፣ የአኅጉሩን የአየር ንብረት ጥበቃ፣ የውሃ ሀብት ጥበቃ፣ የመሬት መልሶ ማቋቋም እና የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የሚያግዝ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ መሆኑን እያረጋገጠ ነው።
ዛሬ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣ እንግዳ ከውይይት በተጨማሪ አረንጓዴ ዐሻራውን አሳርፎ የሚመለሰው። ይህም ከችግኝ በላይ የተተከለው ሐሳብ፣ ከዛፍ በላይ የበቀለው ትብብር እንዲሁም ከዛሬ በላይ የታሰበው የነገ ትውልድ መኖሩን ያረጋግጣል።
በልዩ እሸቱ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: