Search

የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያን የቴክኖሎጂ አቅም ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እየሰራ ነው - ብርጋዲየር ጄኔራል ከበደ ረጋሳ

እሑድ ሐምሌ 19, 2018 41

የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ኢትዮጵያ ወደ ሳይንሳዊ ብቃት እና የቴክኖሎጂ ፈጠራ በምታደርገው ጉዞ ላይ ታሪካዊ ምዕራፍ እያስመዘገበ ነው ሲሉ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ብርጋዲየር ጄኔራል ከበደ ረጋሳ ገለፁ፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ያስገነባውን የላቀ ማዕከላዊ ላብራቶሪ ባስመረቀበት ወቅት የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ብርጋዲየር ጄኔራል ከበደ ረጋሳ፤ ማዕከሉ እጅግ ዘመናዊ የሆነ ላቦራቶሪ ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን የቴክኖሎጂ አቅም የሚያጠናክር እና የ21ኛው ክፍለ ዘመን ፈጣን ተለዋዋጭ ተግዳሮቶችን ለመቋቋም ያለንን ችሎታ የሚያሳድግ ሀገራዊ ስትራቴጂካዊ ሀብትም ጭምር ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ እድገት ሀገራችን ወደ ሳይንሳዊ ብቃት እና የቴክኖሎጂ ፈጠራ በምታደርገው ጉዞ ላይ ታሪካዊ ምዕራፍ እያስመዘገበ ነው ያሉት ጀኔራል መኮንኑ፤ ይህ አስደናቂ ስኬት አዲስ ተቋም ከመክፈት ባለፈ በኢትዮጵያ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መካከል ያለውን ዘላቂ ወዳጅነት፣ እርስ በርስ መተማመን እና ስትራቴጂካዊ አጋርነት የሚያሳይ ምልክት መሆኑን አንስተዋል።

ይህም በእውቀት፣ በፈጠራ እና በሰው ኃይል ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ለዘላቂ ሀገራዊ ልማት እና ለረጅም ጊዜ ደህንነት መሰረት ነው የሚለውን የጋራ ራዕያችንን የሚያንፀባርቅ  ነው ብለዋል።

ለተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መንግስት በተለይም ለተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የመከላከያ ሚኒስቴርን፣ ይህ ማዕከል እውን እንዲሆን ላሳዩት የማይናወጥ ቁርጠኝነት እና ለጋስ ድጋፍ ጥልቅ ምስጋና አቅርበዋል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን የመከላከያ ሚኒስቴር ወክለው መልዕክት ያስተላለፉት ኮሎኔል ዶክተር ካሊድ አላዞሪ ይህንን አስደናቂ እና ታሪካዊ ፕሮጀክት ዳር ለማድረስ የ24 ሰዓት ድጋፍ ስለሰጡ ባለድርሻ አካላት አመስግነው ለኢትዮጵያዊያን ወንድሞቻችን ድጋፍ ለማድረግ ሁሌም ዝግጁ ነን፤ ድጋፋችንም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ይህ ገና ጅምር ነው። ወደፊት በፈጠራ፣ በቴክኖሎጂ እና የኢትዮጵያን ህዝብ አቅም በማሳደግ ረገድ አብሮ ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው መናገራቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ መረጃ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ  ከፍተኛ ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎችን በማፍራት፣ ሁለገብ ምርምሮችን በማበረታታት እና አለም አቀፍ አጋርነቶችን በማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራም ተመላክቷል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: