ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተገነባውን የህጻናትና ወጣቶች ቴአትር ኮምፕሌክስ መርቀው ከፍተዋል፡፡
ሙሉ በሙሉ ለቴአትርና ሲኒማ ዓላማ የተገነባው ኮምፕሌክሱ፤ ለኪነ ጥበብ ስራዎች እንዲመች ዘመኑን በሚመጥን ደረጃ የተገነባ ነው፡፡
መንግስት ባለፉት የለውጥ ዓመታት ትኩረት ከሰጠባቸው ዘርፎች አንዱ ኪነ ጥበብ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኮምፕሌክሱ ተጠናቆ መመረቅ መንግስት ለዘርፉ ያሳየውን ትኩረት እንደሚያሳይ ገልፀዋል፡፡
አዲስ አበባ ለኪነ ጥበብ የምትመች ከተማ እየሆነች መምጣቷን በማንሳትም ይህንን ለሀገር ግንባታ በሚጠቀም መልኩ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
የኪነ ጥበብ ስራዎች ገበያ ተኮር እየሆኑ መጥተዋል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ዘርፉን በዒላማ ሳይሆን በዓላማ መመራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
ኮምፕሌክሱን ከቢሮክራሲ በፀዳ መልኩ በጋራ በመጠቀም አንጋፋዎቹ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ወጣቶችን ሊያሰለጥኑና ጀማሪዎቹን ሊያበረታቱ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በአሸናፊ እንዳለ
#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #AddisAbaba #TheaterComplex