በአይነቱ የመጀመሪያና እጅግ ዘመናዊ የሆነዉ የህፃናትና ወጣቶች ቴአትርና ሲኒማ ኮምፕሌክስ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት ተመርቋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፤ ጥያቄን አዳምጦ ተገቢ ምላሽ መስጠት የመንግስታችን መገለጫ ሆኗል ብለዋል፡፡
ኪነ ጥበብ በተገቢው ሁኔታ የሀገር ግንባታ ሚናውን እንዲወጣ ዘመኑን የዋጀ ቦታ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
በዚህም ጣርያቸው የሚያፈሱና ፍጹም ለፈጠራ ስራ የማይመቹ የኪነ ጥበብ ስፍራዎችን መቀየር መቻሉን ገልፀዋል፡፡
መንግስት እያከናወነ ባለው ሁለንተናዊ የለውጥ ስራ ውስጥ ኪነ ጥበብ አለመዘንጋቱን የጠቆሙት ከንቲባዋ፤ በርካታ ፕላዛዎችና አንፊ ትያትር ቤቶች ገንብተናል ዘርፉን ከዚህ በላይ ለመደገፍም በራችን ክፍት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በሚሰራቸዉ የልማት ስራዎች ሁሉ ኪነ ጥበብን አበይት የትኩረት አቅጣጫዉ አድርጎ እየተገበረ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
በከተማዋ በተተገበረው ሁለንተናዊ ለዉጥ የተለያዩ የዉጭ የኪነ ጥበብ ስራ የሚከወንባቸዉ ከ 160 በላይ አንፊ ቴአትርና ፕላዛዎችን ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውንም ከንቲባዋ ጠቅሰዋል።
ዛሬ የተመረቀው የህፃናትና ወጣቶች ቴአትርና ሲኒማ ኮምፕሌክስ ባለ14 ወለል ህንፃ፣ 2 ዘመናዊ ሲኒማ ቤቶችን፣ የቴአትር አዳራሽ፣ 3 የተለያዩ አዳራሾችን፣ የሆቴል እና ሪስቶ ራት ዘመናዊ ካፍቴሪያዎችን እንዲሁም የፓርኪንግ አገልግሎት ይዟል።
ሙሉ በሙሉ ለቴአትርና ሲኒማ ዓላማ የተገነባው ኮምፕሌክሱ፤ ለኪነ ጥበብ ስራዎች እንዲመች ዘመኑን በሚመጥን ደረጃ የተገነባ ነው፡፡
በአሸናፊ እንዳለ
#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #AddisAbaba #TheaterComplex