ኢትዮጵያ የዓለም ሕዝብ በስስት የሚጎበኛቸው፤ ዩኔስኮ ድንቅነታቸውን የመሰከረላቸው የበርካታ ቅርሶች ባለቤት ናት።
ሀገሪቷ ከሚዳሰሱ እና ከማይዳሰሱ ቅርሶች ልማት በተጨማሪ ሀላላ ኬላ፣ ጨበራ ጩርጩራ፣ ወንጪ፣ ጎርጎራ እና ሌሎችንም የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማትም ከቱሪዝም ኢኮኖሚው ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን ጥረቷን አጠናክራለች።
የኢትዮጵያ አየር መንገድም መንገደኞችን ከተለያዩ ዓለማት ከማጓጓዝ ባለፈ ቱሪዝሙን በመደገፍ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው ተናግረዋል፡፡
አየር መንገዱ የውጭ ዜጎች በቦሌ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ሲተላለፉ አዲስ አበባን ብቻ ሳይሆን የተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎችን እንዲጎበኙ ለማስቻል ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እየሰራ ይገኛል ይላሉ፡፡

ከውጭ ሀገራት የመጡ መንገደኞችን ወደፈለጉት የቱሪስት መዳረሻ ከማጓጓዝ ባለፈ አየር መንገዱ በሚያስተዳድራቸው እና በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በሚገኙ ዘመናዊ ሎጆች እንዲያርፉም ያደርጋል ሲሉ ያስረዳሉ።
በዘመናዊ ሆቴል እና ሎጆቹ አማካኝነትም ለቱሪስቶች ደረጃውን የጠበቀ የሆቴል አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንም ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል፡፡
አየር መንገዱ ቱሪስቶችን ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ በማጓጓዝ በስካይላይት ሆቴል እንዲቆዩ እንዲሁም ወደሚፈልጉት ሎጅ በመውሰድ ኢትዮጵያ ውስጥ ያላቸውን ቆይታ እንዲያራዝሙ በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
አስተማማኝ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት የሀገሪቱን እድገት መደገፍን ዓላማ አድርጎ እየሰራ የሚገኘው አየር መንገዱ፤ የኢትዮጵያን በጎ ገፅታ ለዓለም በማስተዋወቅ፤ የሀገሪቱን ቱሪዝም በማሳደግ እንዲሁም ኢትዮጵያ የኮንፈረንስ እና የንግድ ማዕከል እንድትሆን ገንቢ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም አንስተዋል።
በተጨማሪም የወጪ ንግድን በማሳለጥ፣ የውጭ ምንዛሬን በማስገባት እና ለሀገሪቱ ሁለንታናዊ እድገት ወሳኝ ድርሻውን በመወጣት ላይ ስለመሆኑም ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲስ አበባን ጨምሮ በ23ቱም የሀገር ውስጥ መዳረሻዎች ለደንበኞች የሚሰጠውን የአገልግሎት ጥራት ለማሳደግ እና ለቱሪስቶች አመቺ የሆኑ አነስተኛ አውሮፕላኖችን ለማስመጣት በግዥ ሂደት ላይ መሆኑም ተመላክቷል።
አየር መንገዱ ወደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በቡድን ሆነው ለሚጓዙ መንገደኞች የአየር ትራንስፖርት አገልግሎትን በቅርቡ መስጠት መጀመሩም የሚታወስ ነው።
በላሉ ኢታላ