Search

ከተናጠል ጥረት ይልቅ የጋራ ተሳትፎ ለኢኮኖሚ ዕድገቱ ወሳኝ ነው - ገመቺስ መርሻ (ዶ/ር)

ሰኞ መስከረም 19, 2018 32

የምጣኔ ሃብት ተመራማሪ እና መምህር የሆኑት ገመቺስ መርሻ (ዶ/ር) ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማጎልበት የሀሳብ ልዩነቶችን በማጣጣም ለሀገራዊ ጥቅም በጋራ መሥራት እንደሚገባ ገልፀዋል።
አሰባሳቢ የወል ትርክትን በማጠናከርም የጋራ ልማት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም ነው ያመላከቱት።
ኢትዮጵያ ለግብርና ምቹ የሆነ ለም አፈር፣ ተስማሚ የአየር ፀባይ፣ ለመስኖ የሚሆኑ ወንዞች እና ታታሪ አርሶ አደር አላት ያሉት የምጣኔ ሀብት ተመራማሪው፤ በተቀናጀ መንገድ ግብርናውን በማዘመን እንደሀገር ምርታማነቱን ማሳደግ እንደሚገባም ያነሳሉ።
በተጨማሪ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ የተለያዩ ማዕድናት መኖራቸውን አመላክተው፤ አሰባሳቢ የወል ትርክትን በመጠቀም ሃብቶችን በስፋት ማልማት ይገባል ሲሉም ገልፀዋል።
ሀገር ጠንካራ ሆና እንድትቆም ተባብሮ መሥራት የሁሉም ሰው ሃላፊነት እንደሆነ የሚገልጹት የምጣኔ ሃብት ተመራማሪው ፤ ብልጽግናን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጎናፀፍ ሁሉም ዜጋ በልማቱ ተሳታፊ መሆን እንዳለበትም ነው ያነሱት፡፡
በጋራ ስንቆም እና ሥንሰራ ውጤታማ መሆን እንደምንችል በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ማሳየት ችለናል ብለዋል።
በቀጣይም የጋራ እሴቶችን በጠበቀ መልኩ በትብብር በመሥራት ልማቱን ማፋጠን ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
 
በሜሮን ንብረት