ዓለም አቀፍ የቡና ቀን ዛሬ በተለያዩ ሀገራት እየተከበረ ይገኛል።
የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የቡና ቀን በይፋ የተከበረው እ.አ.አ. ጥቅምት 1 ቀን 2015 በጣሊያኗ ሚላን ውስጥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል በሆነው ዓለም አቀፍ የቡና ድርጅት (ICO) አማካኝነት ነው።
የዘንድሮው ዓመት የቡና ቀን "ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትብብርን ማጠናከር" በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ ይገኛል፡፡

ዕለቱ የቡናን ጥራት እና ተፈላጊነት ለማሳደግ፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቡና አምራቾች፣ ቡና አዘጋጆች፣ ባሬስታዎች እና ሌሎች መተዳደሪያቸውን ቡና ላይ ያደረጉትን መደገፍን ዓላማ አድርጎ ነው እየተከበረ የሚገኘው።
በኢንዱስትሪው ውስጥ ፍትሐዊ ንግድን እና ዘላቂ አሠራሮችን ማስተዋወቅ እንዲሁም አነስተኛ ቡና አምራቾች የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች በመለየት መፍታትም ተደማሪ የዕለቱ ዓላማዎች ናቸው፡፡
በዓለም ቁጥር አንድ ተመራጭ የሆነው አረቢካ ቡና መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ የምርቱን ብዛት እና ጥራት በማሻሻል ከዘርፉ የምታገኘውን ጥቅም ለማሳደግ እየሠራች ትገኛለች፡፡
ኢትዮጵያ በ2017 በጀት ዓመት ብቻ ከ1.2 ሚሊዮን ቶን በላይ ቡና በማምረት 468 ሺህ 967 ሜትሪክ ቶን ቡና ለዓለም አቀፍ ገበያ አቅርባለች። ከዚህም 2.7 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሪ አግኝታለች።
በአረንጓዴ ዐሻራ ትኩረት ከተሰጣቸው ተክሎች መካከል ቡና አንዱ ሲሆን፣ አረንጓዴ ዐሻራ ከጀመረ ወዲህ የቡና ምርትም እያደገ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ብራዚል፣ ቬትናም፣ ኮሎምቢያ፣ ኢንዶኔዥያ እና ኢትዮጵያ የዓለም ከፍተኛ ቡና አምራቾች ሀገራት ናቸው፡፡
በለሚ ታደሰ