የረመዳን ወር በጎ ሥራዎች የሚንፀባረቁበት፣ ሁሉም ሰው ያለውን በማካፈል አብሮነትን በሚያጠናክሩ ሁነቶች በጾም እና በጸሎት የሚበረቱበት ወር ነው።
በአንዋር መስጅድ በየዓመቱ የሚዘጋጀውን የኢፍጣር መርሐ-ግብር ምን ድባብ አለው? ምን ምን ተግባሮችስ እንደሚከናወኑ ኢቢሲ ዶትስትሪም ቅኝት አድርጓል።
ይህ አይነቱ በጎነት ላለፉት አምስት ዓመታት ሳይቋረጥ እየተዘጋጀ መቀጠሉን በአንዋር መስጅድ የበጎ ተግባር ተሳታፊ ወጣቶች ኅብረት አስተባባሪ ሐይደር ዳውድ ነግሮናል።
የወጣቶች ኅብረቱ ከ200 በላይ አስተናጋጆችን በውስጡ ያቀፈ ሲሆን መርሐ-ግብሩ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ምግብ ከማሰናዳት ጀምሮ በኢፍጣሩ ላይ የሚገኙ ሰዎችን መመገብ፣ ዕቃዎችን ማጠብ እና መስጅዱን ማፅዳት ሥራዎችን በትብብር ይሠራሉ።