Search

ኢትዮጵያን ወደ ተሟላ አረንጓዴ ኃይል የሚያሸጋግራት የተፈጥሮ ጋዝ

እሑድ መስከረም 25, 2018 1076

ኢትዮጵያ በሶማሊ ክልል ካሉብ በዓመት 111 ሚሊዮን ሊትር ማምረት የሚችለውን የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ዙር አስመርቃለች።

በተመሳሳይም በዓመት 1.33 ቢሊዮን ሊትር የማምረት አቅም የሚኖረውን ሁለተኛውን ዙር የተፈጥሮ ጋዝ ማምረቻ ፋብሪካ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።

የመጀመሪያ ዙሩን መርቀው ለሁለተኛው ዙር ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) የፕሮጀክቱን ጠቃሚነት የገለጹት፣ "ከፈሳሽ ተፈጥሮ ጋዝ ምርት ባሻገር በኃይል ማመንጫ ዘርፉም 1 ሺህ ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም በመያዝ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ይኖረዋል" በማለት ነው።

ኢትዮጵያ ማምረት የጀመረችው የተፈጥሮ ጋዝ ከኃይል ምንጭነቱ ባሻገርም ለማዳበሪያ ማምረቻ ወሳኝ የሆነውን ግብዓት በማቅረብ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል የምታደርገውን ጉዞ እንደሚደግፍ ተጠቅሷል፡፡

የተፈጥሮ ጋዝ ታዳሽ ካልሆነ (ከበካይ) የኃይል ምንጮች ወደ ታዳሽ የኃይል ምንጮች ለሚደረገው የኢነርጂ ጉዞ እንደ ሽግግር የሚያገለግል የኃይል ምንጭ ነው፡፡

ከነዳጅ ወይም ከድንጋይ ከሰል በጣም ያነሰ የሙቀት አማቂ ጋዞችን (የግሪንሃውስ ጋዝ) የሚያመነጭ እና አነስተኛ የብክለት መጠንም ያለው ነው፡፡

የተፈጥሮ ጋዝ "ሚቴን" ጋዝ የሚገኝ ሲሆን፣ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ዓመታት ውስጥ ከሚበሰብሱት የዕፅዋት እና የእንስሳት ቅሪተ አካላት በባሕር ውስጥ እና በከርሰ ምድር ይፈጠራል።

የተፈጥሮ ጋዝ በዋነኛነት ለሙቀት እና ለመብራት የሚያገለግል ሲሆን፣ የኃይል ማመንጫዎችን ተርባይን በማንቀሳቀስ ውጤታማ እና ወጪ ቆጣቢ ኃይል ለማመንጨትም ያገለግላል፡፡

የተፈጥሮ ጋዝ የኢነርጂ ደኅንነትን በማረጋገጥ፣ ኢኮኖሚያዊ እድገትን በማጎልበት እና በቀጣይ ወደ ተስማሚ የኃይል አማራጭ የሚደረገውን ሽግግር በማመቻቸት ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።

በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በማመንጨት ዓመታዊ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርትን (GDP) የሚደግፍ ሲሆን፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መደበኛ እና ጊዜያዊ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠርም የአገልግሎት ዘርፉን የሚያነቃቃ ነው። 

የተፈጥሮ ጋዝ ከነዳጅ ጋር ሲነጻጸር ለተጠቃሚው ቀጥተኛ የኃይል ምንጭ በመሆን 93 በመቶ ውጤታማ እንደሆነ ነው ጥናቶች የሚያመላክቱት፡፡ 

ለመብራት እና ለቤት ውስጥ ማሞቂያ ለማዋልም የበለጠ ወጪ ቆጣቢ የኃይል ምንጭ ሲሆን፣ ይህም ለአምራቾች እና ለተጠቃሚዎች ወጪን በመቀነስ ረገድ ተፈላጊ እንደሆነ የአሜሪካ "ቻምበር ኦፍ ኮሜርስ" መረጃ ያመላክታል።

እ.አ.አ. በ2021 የዩሮስታት ሪፖርት ላይ እንደተጠቀሰው 32.7 በመቶ የሚሆኑት የአውሮፓ ኅብረት ኢንዱስትሪዎች የኃይል ምንጭ የተፈጥሮ ጋዝ ነው።

የተፈጥሮ ጋዝ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ በጣም አስፈላጊ ከሆኑት የኃይል ምንጮች አንዱ ሲሆን፣ 36 በመቶ የአውሮፓ ኅብረት የኃይል ፍጆታን፣ እንዲሁም 25 በመቶ በላይ የአሜሪካን የኃይል ፍጆታ የሚደግፈው የተፈጥሮ ጋዝ እንደሆነ በተፈጥሮ ጋዝ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሚሠራው የ"MET Group" መረጃ ያመላክታል

ባለሙያዎች እንደሚሉት በተፈጥሮ ጋዝ የሚሰሩ የጭነት መኪናዎች ለረጅም ርቀት ጭነት በማጓጓዝ ረገድ የበለጠ ውጤታማ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ወጪው ከሌላው ነዳጅ ዝቅተኛ በመሆኑ ለኢኮኖሚው የሚያደርገው ድጋፍ ከፍተኛ ነው።

ለዚህ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ዙር ምርቃት እና ሁለተኛ ዙር ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ ማንኛውንም በነዳጅ የሚሰራ ትራክ ወደ ኢትዮጵያ ማስገባት የተከለከለ መሆኑን እና በአንፃሩ ማንኛውም ባለሀብት ጋዝ የሚጠቀሙ የነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪዎች እና ከባድ ተሽከርካሪዎችን የሚያስገባ ከሆነ ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገባ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግለት ያስታወቁት።

በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 2 ሺህ የሚጠጉ ወደአዲስ አበባ ከተማ እና ወደ ክልል የሚሄዱ አውቶቡሶች አሁን ከሚጠቀሙት ነዳጅ ወደ ጋዝ እንሚቀየሩ እና ይህም የትራንስፖርቱን ዋጋ ቢያንስ በግማሽ እንደሚቀንስም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የኢነርጂ ሽግግርን ለማፋጠን የተፈጥሮ ጋዝን ከሌሎች ምንጮች መካከል ማካተት እንደሚገባ ይመክራል።

ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ (LNG) 162 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ቀዝቅዞ ወደ ፈሳሽነት የሚቀየር የተፈጥሮ ጋዝ ነው፡፡ መጀመሪያ ከሚገኘው "ሚቴን" ጋዝ ይዞታ ወደ ፈሳሽነት ሲቀየር ከቀድሞ ይዞታው እጅግ አነስተኛው ፈሳሽ ይሆናል፡፡

ጋዙን ወደ ፈሳሽነት መቀየር ደኅንነቱን በጠበቀ መንገድ ለማጓጓዝ እና ለመጠቀም ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ሲሆን፣ ፈሳሹ ወደሚፈለግበት ቦታ ከደረሰ በኋላ ሙቀትን በመጠቀም ቀድሞ ሁኔታው (ወደ ጋዝነት) ለሚፈለገው አገልግሎት እንዲውል ይደረጋል።

በለሚ ታደሰ

#EBC #ebcdotstream #naturalgas #LNG #GreenEnergy