ማንኛውም አካል የኢትዮጵያን የባህር በር መሻት በቀና መንገድ እንጂ አጣምሞ ሊረዳው እንደማይገባ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለፁ፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከኢቢሲ ኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ኢትዮጵያ ሰላማዊ ባልሆነ መንገድ የባህር በርን ልትወስድ ትፈልጋለች የሚሉ የተሳሳቱ ትርክቶች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑንም ይህንን የተሳሳተ ሀሳብ ማክሸፍ እና እውነታውን ለዓለም ማሳወቅ ይገባል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የባህር በር የምትፈልገው በሰላማዊ መንገድ ብቻ በመሆኑ ጉዳዩን በቀና መንገድ መገንዘብ እንደሚያስፈልግም ነው ያነሱት።
የባህር በር የማግኘት ፍላጎት በሰጥቶ መቀበል መርህ እንዲሁም በዲፕሎማሲ እና በመተባበር መንፈስ የሚሳካ መሆኑንም ነው የገለጹት።
ኢትዮጵያ እያደገች ያለች ሀገር በመሆኗ የወጪ እና ገቢ ንግዷ በስፋት እየጨመረ ስለመምጣቱ የጠቆሙት አምባሳደሩ፤ ይህም የባህር በር አስፈላጊነትን እንደሚያጎላ ነው የተናገሩት፡፡
ትውልዱ የባህር በር አስፈላጊነትን ጠንቅቆ ሊያውቅ ይገባል ሲሉም አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናግረዋል።
በሜሮን ንብረት