የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋናውን የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ለማካሄድ የሚያስችሉ ዝግጅቶችን እያጠናቀቀ መሆኑን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርአያ እንደገለጹት፤ በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ የአጀንዳ ቀረፃ እና የአወያዮች ስልጠና በይፋ ይጀመራል።
የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) አመራሮች በአዲስ አበባ ከኮሚሽኑ ጋር በመወያየት፣ ለትጥቅ ትግል መነሻ የሆኑ ጉዳዮችን ጨምሮ ክልላዊና ሀገራዊ አጀንዳዎቻቸውን በይፋ አስረክበዋል።
ድርጅቱ ያቀረባቸው አጀንዳዎች የተሳሳቱ ትርክቶችን፣ የሕገ-መንግሥት ማሻሻያዎችን እና ተያያዥ ሀገራዊ ጉዳዮችን ያካተቱ ናቸው።

የድርጅቱ ወታደራዊ አዛዥ ኮሎኔል ፈንታው ሙሀባ እና ሌሎች አመራሮች፣ የሰላም አማራጭን መከተል ለሀገር ህልውና ያለውን ፋይዳ በመጥቀስ በጫካ የሚገኙ ሌሎች ታጣቂዎችም ይህን የሰላም መንገድ እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ፕሮፌሰር መሥፍን አርአያ የአፋሕድ አመራሮች ለሀገራዊ ምክክሩ ላሳዩት ቁርጠኝነት አድናቆታቸውን ገልጸው፣ ሂደቱ ሁሉንም ወገኖች ያሳተፈ እና ለዘላቂ መግባባት መሰረት የሚጥል መሆኑን ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ሀገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል ተብሎ ይጠበቃል።
#Ethiopia #Peace #NationalDialogue #ኢትዮጵያ #ሰላም #ሀገራዊምክክር #EthiopianBroadcastingCorporation