የሀገራችን ኩራት ከሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ጋር በጋራ በምንሰራባቸው ጉዳዮች ላይ ዛሬ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።
ኢትዮጵያውያንን ከዓለም ጋር ከሚያገናኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሳውን እና ማኔጅመንታቸውን የወንዝ ዳርቻ እና የኮሪደር ልማትን ካስጎበኘናቸው በኋላ በተደራጀ እና በተቀናጀ መልክ በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመናል ብለዋል ከንቲባዋ።
ስምምነቱ በዋናነት በከተማዋ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻዎች ልማት የለሙ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን የማስተዋወቅ በዚህም “የእግረ-መንገድ ቱሪዝም” (Stopover Tourism) ተጠቃሚነትን ማሳደግ፣ የከተማችን አዲስ መለያ የሆነውን “new face of Africa”ን ማስተዋወቅን ያካትታል ብለዋል።
በተጨማሪም ስምምነቱ የአቪየሽን ደኅንነትን ማረጋገጥ፣ በከተማዋ የተለያዩ ማኅበራዊና ሰው ተኮር ሥራዎችን በጋራ መስራት ላይ ያተኮረ መሆኑንም አስታውቀዋል።
አየር መንገዱ በከተማዋ በምንሰራቸው ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች እና በኮሪደር ልማት ላይ ለነበረዉ ድጋፍ ከልብ እያመሰገንን ፣ የከተማ አስተዳደራችን ለስምምነቶቹ ተፈፃሚነት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ጋር ከከዚህ ቀደሙ በበለጠ ተቀራርቦ የሚሰራ ይሆናል ብለዋል።