ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ትላንት በተካሄደው የታማኝ ግብር ከፋዮች የዕውቅና አሰጣጥ መርሐ ግብር፤ ባለፉት ዓመታት በታማኝነታቸው ለዘለቁ ግብር ከፋዮች ልዩ ዕውቅና ሰጥተዋል።
የወርቅ እና ከዚያ በላይ ተሸላሚ የሆኑ ታማኝ ግብር ከፋዮች ምርጥ ዜጎች ስለሆኑ፤ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲጓጓዙ በ"ቪአይፕ" እንዲስተናገዱ እና እንግልት እንዲቀርላቸው እንደሚደረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
ባለፉት አራት ዓመታት በታማኝነት ግብራቸውን ሲከፍሉ የነበሩ 30 የፕላቲኒየም ደረጃ ተሸላሚ ድርጅቶች ባለቤቶች ወይም ሥራ አስፈጻሚዎች ደግሞ፤ ኢትዮጵያውያን ከሆኑ ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት እንደሚሰጣቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ባለፉት አራት ዓመታት ልዩ የፕላቲንየም ተሸላሚ ሆነው የቀጠሉ ታማኝ ግብር ከፋዮች፤ የኢትዮጵያ ልዩ ኩባንያ ሆነው በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በኢንቨስትመንት እንዲሳተፉ የኢትዮጵያ መንግሥት ልዩ ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስታወቁት።
ኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ ዕድገት እያስመዘገበች ስለሆነ ዕድገቷ በሀገር ውስጥ በቻ ተወስኖ መቅረት የለበትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፥ እነዚህ ኩባንያዎች በተመረጡ የአፍሪካ ሀገራት ብቻቸውን ወይንም ከሌሎች ኩባንያዎች ጋር ሆነው ኢንቨስትመንት ላይ እንዲሳተፉ በየሀገራቱ ያሉ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ድጋፍ ልዩ ያደርጉላቸዋል ብለዋል።
በለሚ ታደሰ