Search

የጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ዕውነታ

ረቡዕ መስከረም 28, 2018 154

ኢትዮጵያ በርካታ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በማከናወን ላይ ናት። በዚህም ለዘመናት ስብራት የነበሩ የኢኮኖሚ ጉዳዮችን በመጠገን በማንሰራራት ላይም ትገኛለች፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ ኢትዮጵያም ፊቷን ወደሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶች አዙራለች። ለደኅንነቷ ወሳኝ ወደ ሆነው የወደብ ባለቤትነት ለመመለስም ጥረቷን ቀጥላለች።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ አዝመራው አንዴሞ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ሕዳሴ ግድብ እና ቀይ ባህር ለኢትዮጵያ ወሳኝ ጉዳዮች ስለመሆናቸው ገልጸዋል፡፡
በታላቁ የሕዳሴ ግድብም ሆነ በወደብ ጉዳይ የተሳሳቱ አመለካከቶች እንዳሉ የጠቀሱት ም/ሰብሳቢው፣ የተሳሳቱ ምልከታዎችን በማጥራት ኢትዮጵያ ግድቡን ገንብታ ለጋራ አፍሪካዊ ጥቅም ማዋል ችላለች ብለዋል፡፡
የባሕር በር በበኩሉ ለሀገሪቷ እድገት ወሳኝ በመሆኑ ኢትዮጵያ ወደብ የማግኘት መብት እንዳላት እና ይህንኑ ጥያቄዋንም አንስታ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ አጀንዳ ማድረግ መቻሏን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄ እና ተጠቃሚነት የቀጣናውን የጋራ ደኅነት ለማረጋገጥ የሚረዳ መሆኑንም ነው ያነሱት።
ለበርካታ ዘመናት ስብራት የነበሩ ጉዳዮች ላለፉት 7 ዓመታት እየተጠገኑ መምጣታቸውን ጠቁመው፣ የምንገኝበት ጊዜ ለኢትዮጵያውያን የድል ብሥራት እያመጣ እና የታሪክ ስብራትን እየጠገነ ያለ ጊዜ ነው ብለዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው፤ በወደብ ባለቤትነት ጉዳይ ለ3 አሥርት ዓመታት የነበሩ ዝምታዎች መሰበራቸውን አንስተዋል።
"በሀገሪቱ እየተሠሩ ባሉ ሥራዎች ወደ ግባችን ማማ እየተጓዝን ነው" ያሉት አምባሳደር ዲና፣ የባሕር በርም ሆነ ሜጋ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን መፃኒ እጣ ፈንታን የያዙ ግቦች መሆናቸውንም ነው ያነሱት።
 
በሜሮን ንብረት