Search

የተሟላ ብልፅግናን ለማምጣት የገጠሩን አኗኗር ዘዬ ማዘመን ግድ ይላል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ረቡዕ መስከረም 28, 2018 136

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በክረምት በጎ ፈቃድ መርሐ-ግብር የተገነቡ ሞዴል የገጠር መንደሮችን ለተጠቃሚዎች አስረክበዋል።
በወቅቱም የእኛ የብልፅግና ትርክት እያንዳንዱን ዜጋ፣ ቤተሰብ እና መንደር ካልነካ የተሟላ አይሆንም ሲሉ ተናግረዋል።
 
በከተሞች የተከናወነው የዘመናዊ መንደሮች ግንባታ ወደገጠር መስፋፋት አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህን ለማሳካት በጎ ፈቃደኞች፣ ባለሃብቶች፣ የመንግሥት ተቋማት እና ኩባንያዎች ነብስን በሚያስደስተው የዘመናዊ መንደር ግንባታ ሊሳተፉ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ከነበረው የኑሮ ዘይቤ ከፍ ያለ የገጠር አኗኗርን የሚከተል፣ የተሻገረ ገጠርን መፍጠር አለብን የሚል ትልም ነበረን፤ ዘንድሮ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ አምስቱም ዞኖች ይህ ሥራ ታይቷል ብለዋል።
 
በዚህም ለገጠሩ ኅብረተሰብ ዘመናዊ የእንስሳት እርባታ እና እርሻ የሚያከናውንበትን ቦታ፣ የባዮ ጋዝ ፣ የፀሐይ ብርሃን ቴክኖሎጂ፣ ዘመናዊ የንፅሕና መጠበቂያዎች እና መሰል አገልግሎቶችን የሚያገኝበትን መንደር መገንባት ተችሏል ሲሉ አስረድተዋል።
በከተማም ሆነ በገጠር የተሻለ ኢኮኖሚ ያላቸውን እና እጅ አጠሩን የሚያቀራርብ አኗኗርን በመፍጠር የተሟላ ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል ሲሉ አስረድተዋል።
አርሶ አደሩን የሚጠቅም የዘመናዊ መንደር ግንባታም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።