የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር አክሲዮን ማኅበር ከሎጂስቲክስ አገልግሎት ባሻገር የባቡር መስመር የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራ መጀመሩ ተገለፀ፡፡
የመጀመሪያው የባቡር መስመር ዝርጋታ ከኤ ኤም ጂ ሆልዲንግስ ኢንዱስትሪ ፓርክ ወደ እንዶዴ ዋናው የጅቡቲ መስመር የሚያገናኝ ግንባታ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል፡፡
የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር)፤ ለባቡር ሃዲድ ግንባታ ፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡
ሚኒስትሩ የባቡር መስመር ዝርጋታው ዲዛይን በኢትዮጵያውያን የተሰራ እና ወጪው የሚሸፈነው በግል ባለሐብት መሆኑ ለየት እንደሚያደርገው በዚህ ወቅት ተናግረዋል፡፡
የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር አክስዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢ/ር ታከለ ኡማ በበኩላቸው፤ የባቡር መስመር ዝርጋታው በሀገር ውስጥ አቅም መሰራቱ ለሌሎች ፕሮጀክቶች ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር አመላክተዋል፡፡
አክለውም አክስዮን ማህበሩ በምስራቅ አፍሪካ ተወዳዳሪ የሚሆን የግንባታ ዘርፍ ማደራጀቱንም ጠቁመዋል፡፡
የባቡር መስመሩ ኤ ኤም ጂ ሆልዲንግስ ኢንዱስትሪ ፓርክ ወጪና ገቢ ምርቶችን በቀላሉና በፍጥነት ለማመላለስ የሚጠቅመበት እንደሆነ የድርጅቱ ባለቤትና ዋና ሥራ አስፈፃሚ አብዱልሀኪም መሐመድ ገልፀዋል፡፡
ግንባታው በስድስት ወራት ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን የባቡር መስመሩ ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረውም ተጠቅሷል፡፡
በመሐመድ ራህመቶ