Search

ዲጂታላይዜሽን ቀጣናውን በማስተሳሰር ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል - አቶ አህመድ ሽዴ

ሓሙስ መስከረም 29, 2018 68

ዲጂታላይዜሽን የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጣናን በማስተሳሰር ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ገለጹ።

አቶ አህመድ በናይሮቢ፣ ኬንያ የተካሄደውን 24ኛው የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (COMESA) የመሪዎች ጉባዔ በሚመለከት በሰጡት ማብራሪያ፥ የጉባዔው ዋና አጀንዳ በሆነው ዲጂታላይዜሽን ላይ አመርቂ ውጤት እያመጣች ያለችው ኢትዮጵያ ልምዷን አካፍላለች ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባዔው ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ኢትዮጵያ የዲጂታል መሠረተ ልማትን በመዘርጋት ረገድ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቧን መግለጻቸውን ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።

የዲጂታል ዘርፉ በአሁኑ ወቅት ለኢትዮጵያ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያበረከተ እንደሚገኝ ያወሱት አቶ አህመድ፤ በተለይ በፋይናንስ ዘርፉ ዲጂታላይዜሽን ራሱን የቻለ ስትራቴጂ ያለው በመሆኑ በከፍተኛ ደረጃ ማደጉን አክለዋል።

ኢትዮጵያ ከጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሱዳን እና ሶማሊያ ጋር እያደገ ያለ የዲጂታል መሠረተ ልማት ግንኙነት እንዳላት ጠቅሰው፤ ይህን ግንኙነት ይበልጥ የማጎልበት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።

ከ24ኛው የኮሜሳ የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣናን የማስጀመር ሥራ መከናወኑን አንስተው፤ ይህም የኢትዮጵያ የሪፎርም ሥራ አንዱ አካል እንደነበር አክለዋል።

የአፍሪካ ሀገራትን የንግድ ልውውጥ በማሳደግ ረገድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆኑንም አቶ አህመድ በማብራሪያቸው ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በአጠቃላይ የአፍሪካን ትስስር በማጠናከር ቀዳሚ ናት ያሉት ሚኒስትሩ፤ ሀገሪቱ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በመሠረተ ልማት ላይ እያከናወነችው ያለው ሰፊ ሥራ በዚህ ረገድ ያላትን አቅም ይበልጥ እንደሚያሳድገው ገልጸዋል።

በሃይማኖት ከበደ

#ebcdotstream #COMESA #Nairobi #Ethiopia