Search

የኑክሌር ኃይል ለኢትዮጵያ ትልቁ የሣይንስ እና ቴክኖሎጂ ርምጃ ነው፡- የኑክሌር ፊዚክስ ምሁር

ዓርብ መስከረም 30, 2018 34

 
ኢትዮጵያ ውስጥ ከገቡ ቴክሎጂዎች የኑክሌር ኃይል ፕሮጀክት ዕቅድ በተለይም ለተለያዩ ዘርፎች ከሚያበረክተው አስተዋፅኦ አኳያ ትልቁ ርምጃ ነው ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኑክሌር ፊዚክስ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር ጥላሁን ተስፋዬ ገለፁ፡፡
በብዙዎች ዘንድ የኑክሌር ኃይል ለጦር መሳሪያነት ብቻ እንደሚውል ተደርጎ ቢታሰብም፤ ለጤና፣ ለግብርና ብሎም ከካርቦን ነጻ የሆነ አስተማማኝ ኃይል ለማግኘት ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው የኑክሌር ፊዚክስ ምሁሩ ከኢቢሲ አዲስ ቀን መሰናዶ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡
ቴክኖሎጂው በመንግስት ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራበት የመጀመሪያው ቢሆንም፤ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ1957 የተቋቋመው የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ አባል መሆኗን አስታውሰዋል፡፡
ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ቴክኖሎጂው በትንሽ ኃይል ግዙፉ የሆኑ ቁሶችን ማንቀሳቀስ የሚችል፣ በተለይም ከሌሎች የኃይል ማመንጫ መንገዶች ጋር ሲነፃፀር ለዓየር መበከል ዝቅተኛ አስተዋፅኦ ያለው እንዲሁም የሚያመነጨው የኃይል መጠን ወጥ እና አስተማማኝ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የኑክሌር ኃይል ወሳኝ የሆኑ ዘርፎችን ከፍታ ላይ የማስቀመጥ አቅም እንዳለው ገልጸው፤ ለኢኮኖሚያዊ እድገት አበርክቶው የጎላ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ለዚህ ተጠቃሚነት የሚያበቃው ውጥን እንዲሰምር ተጠባቂ በሆኑ ተግዳሮቶች እንደ ከፍተኛ የሆነ የመገንቢያ ወጪ ማዘጋጀት፣ ቴክኖሎጂው አዲስ በመሆኑ በዘርፉ የበቁ ባለሙያዎችን ማፍራት ብሎም ማህበረሰቡ ስለ ዘርፉ ያለውን መረጃ ከፍ ማድረግ ላይ መሰራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
 
በአፎሚያ ክበበው