Search

ልዩ ዕውቅና የሚያሰጠው ታማኝ ግብር ከፋይነት

ዓርብ መስከረም 30, 2018 546

ባደጉ ሀገራት የሚገኙ ግብር ከፋዮች ግብር በመክፈላቸው የሚሰማቸውን ኩራት ሲናገሩ ይሰማሉ፡፡ የኩራታቸው ምንጭም እነሱ የሚከፍሉት ግብር ለሀገር ዕድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ማየታቸው ነው፡፡

ግብር ሲከፈል ሀገር ታድጋለች፤ ግብር ከፋዮች ደግሞ ግዴታቸውን በመወጣታቸው መብታቸውን የመጠቀየቅ ሞራልም ይኖራቸዋል፡፡

ሀገር በምትሰበስበው ገቢ በምትሠራቸው መሰረተ ልማቶች ዕድገቷ ሲፋጠን የኩባንያዎች ገቢ እና ትርፍም እያደገ ይሄዳል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(/) የታማኝ ግብር ከፋዮች ዕውቅና አሰጣጥ መርሐ ግብር ላይ እንዳስታቁት፣ በተከታታይ በታማኝነታቸው ለዘለቁ ግብር ከፋዮች ልዩ ዕውቅና ይሰጣል፡፡

ከነዚህ ልዩ ዕውቅናዎች መካከልም ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት፣ የአየር መንገድቪአይፒመስተንግዶ እና በውጭ ሀገር የሚመቻች ልዩ የኢንቨስትመንት ዕድል ይገኛሉ፡፡

እነዚህ ዕውቅናዎች በተለይም የመጀመሪያዎቹ ለከፍተኛ የሀገር ባለሥልጣናት እና ዲፕሎማቶች የሚሰጡ ቢሆንም፣ ለሀገራቸው የታመኑ ግብር ከፋዮችም ከፍተኛውን ኃላፊነታቸውን ስለተወጡ ይገባቸዋል በሚል ነው ዕውቅናው የተሰጣቸው፡፡

የተለያዩ ሀገራትም ለታማኝ ግብር ከፋዮቻቸው የተለያዩ ደረጃ ያላቸው ዕውቅና እንደሚሰጡ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ለመሆኑ ሀገራት ለታማኝ ግብር ከፋዮቻቸው ምን ዓይነት ዕውቅናዎችን ይሰጣሉ?

በርካታ ሀገራት ታማኝ ግብር ከፋዮቻቸውን ለማበረታታት ልዩ የግብር ከፋይ እውቅና ፕሮግራሞችን ይጠቀማሉ።

እነዚህ ፕሮግራሞች ዓመታዊ ሥነ የዕውቅና ሥነ-ሥርዓቶችን እና አልፎ አልፎ ደግሞ ልዩ ጥቅማጥቅሞችን ያካትታሉ።

እነዚህ ሀገሮች ለታማኝ ግብር ከፋዮች የታክስ ማበረታቻዎችን ወይም የተለያዩ የታክስ አያያዝ አማራጮችን ይሰጣሉ፡፡ እነዚህ ታማኝ ግብር ከፋዮች በልዩ ሁኔታ በተመረጡ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ የኢንቨስትመንት ዕድል እንዲያገኙም ይመቻችላቸዋል።

እንደ ስፔን ባሉ ሀገራት ዕውቅና የተሰጣቸው ግብር ከፋዮች ከትርፋቸው የተወሰነውን ለሚፈልጉት ማኅበራዊ አገልግሎት እንዲያውሉ የሚፈቀድላቸው ሲሆን፣ ይህም በሰጡት ማኅበራዊ አገለግሎት ክብር እንዲያገኙ ያደርጋቸዋል፡፡

ለግብር ከፋዮቻቸው የዕውቅና መርሐ ግብር ከሚያዘጋጁ ሀገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ስትሆን፣ ገቢዎች ሚኒስቴር በሚያቀርበው መረጃ መሰረት ዓመታዊ የግብር ከፋዮች የዕውቅና ፕሮግራም ይካሄዳል።

ኢትዮጵያ ለታማኝ ግብር ከፋዮቿ የምትሰጠው ዕውቅና በአስተዋጽኦዋቸው ደረጃ በፕላቲነም፣ በወርቅ እና በብር ደረጃ የተከፋፈለ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም ፕሬዚዳንቱ በሚገኙበት ሥነ ሥርዓቱ ይከናወናል።

ዓላማውም ግብር ከፋዮች ለሀገር እድገት ላበረከቱት አስተዋፅዖ እውቅና መስጠት እና ሌሎችም ይህን አርዓያነት በመከተል ለሀገራቸው ታማኝ እንዲሆኑ ማነሳሳት ነው።

ላይቤሪያም እንደ ኢትዮጵያ ለግብር ከፋዮች ዕውቅና የምትሰጥ ሀገር ነች፡፡ የላይቤሪያ ገቢዎች ባለስልጣን (LRA) ዓመታዊ የግብር ከፋይ ዕውቅና እና ሽልማት መርሐ ግብር አለው።

ግብር ከፋዮች በታማኝነት ግብራቸውን ለመክፈል ለሚያሳዩት ተግባራዊ ቁርጠኝነት የተለያዩ ደረጃዎች ያላቸው ዕውቅናዎች እና ሽልማቶች ይሰጧቸዋል።

በልዩ ሁኔታ የተመረጡ የላያቤሪያ ታማኝ ግብር ከፋዮቹም ብዙውን ጊዜ ልዩ ዕውቅና እና የአንድ ዓመት ከታክስ ነጻ የምስክር ወረቀት ያገኛሉ።

እንደ ካምቦዲያ ያሉ ሀገሮች ደግሞ ለወርቅ ደረጃ ታማኝ ግብር ከፋዮች ለተወሰነ ጊዜ ከውስን ወይም ከዴስክ ኦዲት(desk audits) ነፃ የሚያደርግ የታክስ ተገዢነት የምስክር ወረቀት ያገኛሉ።

እንደ ፓኪስታን ያሉ ሀገራት ደግሞ ለታማኝ ግብር ከፋዮቻቸው በየአር መንገዳቸው ሲጓዙ ቪአይፒእንዲስተናገዱ ያደርጉአቸዋል፡፡ ይህም በየር መንገድ ባሉ ላውንጆች ቪአይፒ አገልግሎት ማግኘትን፣ እንዲሁም ፈጣን የኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ አገልግሎትን ያካትታል፡፡

እንደ የተባበሩት ዓረብ ኢሜሬቶች ያሉ ሀገራት ለታማኝ ግብር ከፋይ ዜጎቻቸው የዲፕሎማቲክ፣ ልዩ እና የሚስዮን ፓስፖርቶችን ይሰጣሉ፡፡

በለሚ ታደሰ