Search

የኩታ ገጠም እርሻ ምርታማነትን ከ30 በመቶ በላይ ማሳደግ አስችሏል - አቶ አዲሱ አረጋ

ቅዳሜ ጥቅምት 01, 2018 50

የኩታገጠም እርሻ ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ትልቅ ሚናን እየተጫወተ መሆኑን የግብርና ሚኒስትሩ አቶ አዲሱ አረጋ ገለጹ።

አቶ አዲሱ ከፌደራል እና ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በጉራጌ ዞን፣ በአበሽጌ ወረዳ እና በቀቤና ልዩ ወረዳ  በኩታ ገጠም እየለሙ ያሉ የበቆሎ እና የጤፍ ማሳዎችን ጎብኝተዋል።

ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የኩታገጠም እርሻ ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

በዘንድሮው የመኸር እርሻ ከ20 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ተሸፍኗል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ከዚህ ውስጥ 12.3 ሚሊዮን የሚሆነው በኩታገጠም እርሻ  የለማ መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን ላይ በሀገሪቱ በስፋት እየተሠራበት የሚገኘው የኩታ ገጠም እርሻ ምርታማነትን ከ30 በመቶ በላይ ማሳደግ አስችሏል ብለዋል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርና ቢሮ ኃላፊ ኡስማን ስሩር በበኩላቸው፥ በክልሉ በመኸር እርሻ ከለማው 564 ሺህ ሄክታር መሬት ከ54 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

በወንድወሰን አፈወርቅ

#ebcdotstream #centralethiopia #ኩታገጠምእርሻ